በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ህገ-ወጥ የሰዎችና የመሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል የተጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው

76

ኢዜአ ህዳር 28 ቀን 2012 በሶማሌ ክልልና በሶማሌ ላንድ አዋሳኝ ድንበሮች ህገ-ወጥ የሰዎችና የመሳሪያ ዝውውርን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ መሆኑን የሶማሌ ክልል የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አብደላሂ መሐመድ ተናገሩ።

የአገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ ዕዝ አዛዦች፤ የሶማሌ ላንድና የሶማሌ ክልል የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ዛሬ በድሬዳዋ ባደረጉት ውይይት በአዋሳኝ ድንበሮች አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን የጀመሩትን ተግባር እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የሶማሌ ክልል የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አብደላሂ መሐመድ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በአገር አቀፍ ደረጃ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ሰፍኗል፡፡

"የተገኘው ሰላም በፀረ-ሰላም ኃይሎች እንዳይበረዝ በምስራቅ የአገሪቱ ክፍልች በፀጥታ ኮማንድ ከሚከናወኑ ተግባራት ጎን ለጎን ከሶማሌ ላንድ ጋር የፀጥታ ኮሚቴ በማቋቋም ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል፡፡

በተለይ ህገ-ወጥ የሰዎችና የመሳሪያ ዝውውርን እንዲሁም የኮትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በጋራ ለመከላከል በተሰሩ ሥራዎች የተሻለ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጋራ ኮሚቴው ፈጣን መረጃዎችን በመለዋወጥ ወደ አገር ሊገባ የነበሩ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለፁት ደግሞ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር መሐመድ አህመድ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ሰፊ የጋራ ድንበር ያላት በመሆኑ አልሸባብም ሆነ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ክፍተት አግኝተው ጥፋት እንዳያደርሱ ለማድረግ ኮሚቴው ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

"የጋራ ኮሚቴ ከተዋቀረ በኋላ በርካታ የአልሸባብ አባላት ተይዘዋል፤ ህገ-ወጥ ተቀጣጣይ መሳሪዎችና ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር አውለናል፤ በህገ-ወጥ መንገድ በስደት ሊወጡ የነበሩ ዜጎችንም ለማትረፍ ችለናል"ብለዋል፡፡

እንደምክትል ኮሚሽነሩ ገለፃ የጋራ ድንበሮችንና አካባቢዎችን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ በየሦስት ወሩ የሚኪያሄደው ውይይት ውጤት እያስገኘ ነው፡፡

የምስራቅ ዕዝ መከላከያ ሠራዊት የዘመቻ መምሪያ ዋና ኃላፊ ኮሎኔል መንገሻ ፋንታሁን በበኩላቸው የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ውስብስብ የፀጥታ ችግር ያለበት ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለፀጥታ ስጋት የሆነው ከፍተኛ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያና የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ህገ-ወጥ ንግድ የሚኪካሄድበት በመሆኑ በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ውይይቱ መሠረታዊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"ኮሚቴው ፈጣን መረጃ በመለዋወጥ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል" ሲሉም ኮሎኔል መንገሻ ገልጸዋል፡፡

እንደእርሳቸው ገለጻ እስከአሁን ድረስ ድንበር ተሻግረው በህገ-ወጥ ሊጓዙ የነበሩ 2ሺህ 400 ሰዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፤ ሰባት ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የተከናወኑ እነዚህ ስራዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም፣ የጋራ ልማትና በልጽግና እንዲሰፍን የምታከናውነውን ተግባር እንደሚያግዙም ነው ኮሎኔሉ ያስረዱት፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሶማሌ ላንድ ተወካይ ሜጀር ጀኔራል ኑር ዑስማኤል ታኒ "ጣምራው ኮሚቴ የርስ በርስ ትብብርን በማዳበር በጋራ ድንበሮች የሚስተዋሉ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ተግባራትን በጋራ ለመመከት አግዟል" ብለዋል፡፡

በቀጣይ የተሻለ ውጤታማ ሥራ ለመስራት በድሬዳዋ የተኪያሄደው ውይይት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ የሶማሌ ላንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በድሬዳዋ አስተዳደር የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም