የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በህዳሴው ግድብ የሚኒስትሮች ስብሰባ ለመሳተፍ ዋሽንግተን ዲሲ ገቡ

48

ኢዜአ ህዳር  28/12 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስቱ አገራት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ዋሽንግተን ዲሲ ገብተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ዋሽንግተን ሲገባ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋና የኤምባሲው ዲፕሎማቶች አቀባበል አድርገውለታል።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአሜሪካ ጋባዥነት ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ባደረጉት ስብሰባ አገራቱ በግድቡ ዙሪያ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይተው ከስምምነት ላይ ለመድረስ ቀነ ገደብ አስቀምጠው ነበር።

የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከቴክኒክ ስብሰባው በተጨማሪ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም እና ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን በሚካሄደው ስብሰባ በመገኘት ስምምነቱ የደረሰበትን ለመገምገምና የውይይቱን ሂደት ለመደገፍ መስማማታቸውም ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከሚያደርጉት ስብሰባ የመጀመሪያው ነገ ዋሺንግተን ላይ ይካሄዳል።

የነገው ውይይት በቅርቡ አዲስ አበባ እና ካይሮ በተካሄዱት የሶስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባዎች በግድቡ ሙሌትና ሌሎች ያልተቋጩ ነጥቦች ላይ ያተኩራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ይሳተፋሉ።

ሁለተኛው የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም