ጉባዔው አትሌት ደራርቱ ቱሉን የፌዴሬሽኑ የበላይ ኃላፊ አድርጎ በመሾምና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

81

ኢዜአ ህዳር  28/12 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ አትሌት ደራርቱ ቱሉን የበላይ ኃላፊው አድርጎ ሲሾም፤ ለስፖርቱ እድገት አስተዋጽኦ አበርክተዋል ያላቸውን አካላት በመሸለም ተጠናቀቀ።

ፌዴሬሽኑ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 23ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አጠናቋል።

የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉን በተቀዳሚ ምክትል ፕሪዚዳንት ማዕረግ ፌዴሬሽኑን በበላይነት እንድትመራ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ይሁንታ ተገኝቷል።

ይህ የሆነው ኃይሌ ገብረስላሴ ሁለት ዓመት ጊዜ እየቀረው ባለፈው ዓመት ራሱን ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት ማግለሉን ተከትሎ ነው።

በዚሁ መሰረት አትሌት ደራርቱ ቱሉ በምክትል ፕሪዚዳንት ማዕረግ ፌዴሬሽኑን በበላይነት እየመራች እስከ መጪው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የምትዘልቅ ይሆናል።

በሌላ ዜና ጉባዔው ለአትሌቲክስ ስፖርት እድገት አስተዋጽኦ አበርክተዋል ላላቸው አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ አትሌቶችና ባለሙያዎች ሽልማትና እውቅና ሰጥቷል።

ከተሸላሚዎቹ መካከል አትሌቲክሱን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደረጉ የነበሩትና አሁን በሕይወት የሌሉት የቀስተ ደመና ስፖንጅ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አቢሴሎም ይህደጎ ይገኙበታል።

የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ደረርቱ ቱሉ፣ የቀድሞ አትሌትና አሁን አሰልጣኝ የሆኑት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ እና የ102 ዕድሜ ባለጸጋው አንጋፋው አትሌት ሻምበል ባሻ ዋሚ ቢራቱ የ50 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በተመሳሳይ አትሌቶቹ ለተሰንበት ግደይ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ሙክታር እንድሪስና ዮሚፍ ቀጄልቻ ባስመዘገቡት ስኬት እያንዳንዳቸው 20 ግራም ወርቅ ተሸልመዋል።

እነዚህን አትሌቶች ያፈሩና ምርጥ የተባሉ አሰልጣኞችና ክለቦችም ተሸላሚ ሆነዋል።

እንዲሁም የቴክኒክ ዳይሬተክሩ አቶ ዱቤ ጅሎና የጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ቢልልኝ መቆያ እያንዳንዳቸው የ20 ግራም ወርቅ ሸልማቱን ተቋድሰዋል።

ባለፈው 2011 ዓ.ም በአትሌቲክስ ስፖርት ስኬታማ ለነበሩ ከልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ለክለቦች የማበረታቻ የገንዝብ ሽልማት ተሰጥቷል።

ከክለቦች መከላከያ ቀዳሚ በመሆን የ300 ሺህ ብር፤ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሁለተኛ ደረጃ በማግኝት የ240 ሺህ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል።

ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅደም ተከተል ሶስተኛና አራተኛ በመሆን የ180 ሺህ እና የ140 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ባለፈው ዓመት ውጤታማ ከነበሩ ክሎችና ከተማ አስተዳደሮች ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች የ240፣ 180 እና የ140 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

በሽልማቱ እስከ ስምንተኛ ደረጃን የያዙ ሌሎች ክለቦችና ክልሎችም እንደየደረጃቸው ተሸልመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም