አብን የአማራ ን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

67
ኢዜአ ህዳር  28/12 የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአማራን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ የህዝቡን መብትና ጥቅም ለማስከበር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ንቅናቄው በመጪው ምርጫ ብርቱ ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል። አብን በደብረ ማርቆስ ከተማ ዛሬ ህዝባዊ ውይይት አካሄዷል። የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በህዝባዊ የውይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት አብን የአማራን ህዝብ ህልውና ለማስከበር ተደራጅቶ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። "አማራ ተደራጅቶ መንቀሳቀሱ ሌላውን ለማጥቃትና ለመጉዳት ሳይሆን የራሱን መብትና ጥቅም በማስከበር ከሌሎች ጋር እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ነው" ብለዋል። የንቅናቄውን ዓላማና የመጨረሻ ግብ ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ሕብረተሰቡ በየአካባቢው ተደራጅቶ ለማንነቱ መከበር እንዲታገልና መብቱ እንዲጠበቅ ለማድረግ መሆኑንም ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል። እንደሊቀመንበሩ ገለጻ ንቅናቄው በመጪው ምርጫ ህዝቡን ከጎኑ በማሳለፍ ብርቱ ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ አበክሮ እየሰራ ነው። የአማራ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን ለጭቁን ህዝቦች ነፃነት መከበር ተምሳሌት መሆኑን አስታውሰው፣ "ህዝቡ በአበረከተው አስተዋጽኦ ልክ ዋጋ እየተከፈለው አይደለም" ብለዋል። የአማራ ህዝብ አሁን ያለው አገራዊም ሆነ ክልላዊ ለውጥ እንዲመጣ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል። ነገር ግን አሁንም በርካታ ውስብስብ ችግሮችን እያስተናገደ መሆኑን ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል። "እየተስተዋለ ያለውን የህልውና አደጋ ለመቅረፍ መላው የአማራ ህዝብ ተደራጅቶ ሊንቀሳቀስ ይገባል" ሲሉም ዶክተር ደሳለኝ አሳስበዋል። በመድረኩ የተሳተፉት አቶ ተስፋ ታደለ በበኩላቸው "ለህዝቡ ደህንነት ሲባል አብን ተጠናክሮ መንቀሳቀስና ህዝቡንም ማንቃት ይኖርበታል" ብለዋል። አብን የህዝቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግ መብቱና ጥቅሞቹ እንዲከበር ለማድረግ የጀመረውን ሥራ ማጠናከር እንዳለበት የገለፀው ደግሞ ወጣት ንብረት ካሴ ነው። በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኘው ቤተ መንግስት አዳራሽ በተካሄደው ውይይት የከተማውና አካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም