የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የአገሪቷን ክልሎች እና ሕዝቦች የፈረጀ ነበር - ፖለቲከኞች

51

ኢዜአ ህዳር  28/12 በኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የፌዴራሊዝም ሥርዓት የአገሪቷን ክልሎች እና ሕዝቦች የፈረጀ እንደነበር ፖለቲከኞች ገለጹ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 'የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ትናንት፣ ዛሬና ነገ' በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና የሃሳብ አራማጆች /አክቲቪስቶች/ ተሳትፈዋል።

የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የሶማሌና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በፌዴራል መንግስት መዋቅር ላይ የከፍተኛ ስልጣን ባለቤት እንዳይኖራቸው አድርጎ መቆየቱን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

በተለይም በአገሪቷ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውሳኔ የሚሰጡት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ አራት ፓርቲዎች መሆናቸውን ጠቅሰው አምስቱ የግንባሩ አጋር ፓርቲዎች ግን የውሳኔው አስፈጻሚ ሆነው መቆየታቸውን አብራርተዋል።

ባለፉት ጊዜያት በአገሪቷ ሲተገበር የቆየው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተቋማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳልነበረም የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የፌዴራል ሥርዓቱ የአገሪቷን ሕዝቦች በተለያየ መንገድ የፈረጀና የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ የስልጣን እርከን በጥቂት ቡድኖች ብቻ እንዲያዝ ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ከአገሪቷ የቆዳ ስፋት 51 በመቶ የሚሆነውንና 30 ሚሊዮን ሕዝብ ያላቸውን የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የሶማሌና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያገለለ እንደነበረም ነው የገለጹት።

"ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው ባለ ሁለት አሃዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት የግንባሩ አጋር ፓርቲዎችን ያገለለ ነበር" ያሉት ተሳታፊዎቹ ከዘጠኙ ክልሎች የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በአገሪቷ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሲያሳልፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ዓላማ ያደረገ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለመዘርጋት ግብ ቢቀመጥም ባለፉት 27 ዓመታት ግን ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር የሚጣረሱ ጉዳዮች ሲተገበሩ መቆየታቸውንም አንስተዋል።

በተለይ 'እኔ አውቅልሃለሁ' የሚባል አካሄድ ለፌዴራል ሥርዓቱ አደጋ ሆኖ መቆየቱ ነው የመድረኩ ተሳታፊዎች የገለጹት።

"የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የአገሪቷን ሕገ መንግስት ሳይሆን የኢህአዴግን ፕሮግራም መሰረት ያደረገ ነበር" ብለዋል።''

በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ ሕገ መንግስትና የፌዴራል ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል የሚሉ ቡድኖች የሚያራምዱት አቋም ከእውነት የራቀ እንደሆነም የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የፌዴራል ሥርዓት የተወሰኑ ቡድኖች የሚመሩትና የሚወስኑበት ሥርዓት እንደነበረም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ መሸጋገር በአገሪቷ ትክክለኛ የፌዴራል ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

በተለይ በፓርቲ ፕሮግራምና በመንግስት መዋቅር መካከል ልዩነት እንዳለ በግልጽ ለማሳየት የሚረዳ መሆኑን በመጥቀስ።

በአሁኑ ወቅት ዴሞክራሲያዊ፣ ሕብረ ብሔራዊና የሕግ የበላይነትን የሚቀበል የፌዴራል ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የፌዴራል ሥርዓቱ የግለሰቦችና የሕዝቦችን እኩልነት ያከበረ ሊሆን እንደሚገባውም የመድረኩ ተሳታፊዎች አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም