የባሕል አውደ-ርዕዩ የባሕልና የገበያ ትስስር እየፈጠረ ነው

140
ኢዜአ ህዳር  28/12 የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን አስመልክቶ በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የባሕል አውደ -ርዕይ የባሕልና የገበያ ትስስር እየፈጠረ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናገሩ። በኦሮሞ ባህል ማዕከል በመካሄድ ላይ ባለው አውደ ርዕይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ብሔረሰቦች አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎች፣ የተለያዩ የምግብ አይነቶችና ሌሎች መገለጫዎቻቸውን ይዘው ቀርበዋል። አቶ ሙሳ ሙሃመድ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎችና ሌሎች የብሔረሰቡን መገለጫዎች በባህል አውደ ርዕዩ አቅርበዋል። አቶ ሙሳ የመጡበትን አካባቢ ባህላዊ አልባሳትና መገልገያዎች ለጎብኚዎች ማቅረባቸው የተለየ ስሜት ፈጥሮባቸዋል። ባህልና እሴቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ባህልና አለባበስ በአንድ ቦታ ማየታቸውም አግራሞት እንደፈጠረባቸው ነው የተናገሩት። ከአማራ ክልል የመጡት ዲያቆን ተጻፈ ታምር ደግሞ በክልሉ የሚታወቁ የተለያዩ ቅርጻቅርጾችን ይዘው ነው በአውደ-ርዕዩ እየተሳተፉ ያሉት። በ13ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የባህል አውደ-ርዕይ መሳተፋቸው ደንበኞችን እንዲያፈሩ አስችሏቸዋል። የኢትዮጵያዊያን ቋንቋ ፣ አለባበስ፣ መገልገያዎችና ሌሎች መገለጫዎችን ማወቅ ከአውደ-ርዕዩ ያገኙት ሌላው ጥቅም መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም ምርቶቻቸውን ወደተለያዩ ክልሎች በመላክ እንዲሸጡ ትስስር እየፈጠርን ነው ብለዋል። በአውደ-ርዕዩ የተለያዩ ብሔረሰቦችን አልባሳት ይዛ የቀረበችው ወጣት ኪያ ሃቢብ የዘንድሮ ተሳትፎዋ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ባህሏን ከማስተዋወቅ ባሻገር ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ተሳታፊዎችን ባህል በአንድ ቦታ ማየቷ ደስታን እንደፈጠረላት ነው የተናገረችው። የተለያዩ ብሔረሰቦች መገለጫ አልባሳትን ይዛ መቅረቧ ጎብኝዎች የፈለጉትን አማርጠው እንዲገዙ አስችሏል ብላለች። በባሕል አውደ-ርዕዩ ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ አብዲ መሃመድ አልባሳትና የተለያዩ ብሔረሰቦች  መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን በአንድ ቦታ ማግኘት ባሕልን ለማወቅ ይረዳል ይላሉ። ካሁን ቀደም አይተውት የማያውቁት ቁሳቁስ፣ አልባሳት፣ እጣንና ሌሎችንም በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ሕዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም የተከፈተው የባሕል አውደ-ርዕይ በመጪው ማክሰኞ ይጠናቀቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም