በዓሉ ኢትዮጵያዊያን የሚተዋወቁበት፣ የሚቀራረቡበትና አንድነታቸውንም የሚያፀኑበት ነው

68
ኢዜአ ህዳር  28/12 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያዊያን የሚተዋወቁበት፣ የሚቀራረቡበትና አንድነታቸውንም የሚያፀኑበት እንደሆነ በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች አዲስ አበባ የገቡ እንግዶች ተናገሩ። 14ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለመታደም እንግዶች ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ተነስተው አዲስ አበባ ከትመዋል። መዲናዋም እንደወትሮዋ ሁሉ እንግዶቿን በኢትዮጵያዊ ባሕሏ ማስተናገዷን ተያይዛዋለች። ኢዜአ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው እንግዶች በዓሉ የኢትዮጵያዊያን የቀደመ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የአንድነትና የበርካታ እሴቶች መታያ ነው ይላሉ። ከደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን የመጡት አቶ ዘሪሁን ተክሌ በዓሉ ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በመጡ ክልሎች የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን የሚሰባሰቡበት በመሆኑ ፍቅርን፣ አንድነትንና መከባበርን የሚፈጥር ነው ብለዋል። የበዓሉ መከበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለውን የመከባበርና ተቻችሎ የመኖር እሴት እየሸረሸረ የመጣውን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ያልሆነ ድርጊት ትተን የቀደመ የአብሮነት እሴታችንን ለመመለስ ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት ደግሞ ከጋሞ የተገኙት የዘይሴ ማህበረሰብ አባል አቶ ኢሳያስ ቦሊሴ ናቸው። በዓሉ ትውፊቶቻችን እንዳይበረዙና ኅብረ ብሔራዊነታችን ለዓለም ሕዝቦች መስህብ ሆኖ እንዲታይ የማድረግ ኃይልም አለው ብለዋል። ከአርባምንጭ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ሠራዊት ታደሰም ዕለቱ በአገራችን ያሉ የማናውቃቸውን ቋንቋዎች፣ አልባሳት፣ ባህላዊ ጭፈራዎች እና የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን የሚያሳይ፤ አንድነታችንን የምናጠናክርበትንም ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል። ከትግራይ ክልል የመጡት አቶ ብርሃኑ ገብረኪዳን ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኢትዮጵያዊያን የሚተዋወቁበት፣ የሚቀራረቡበት፣ የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያሳድጉበትና አንድነታቸውንም የሚያፀኑበት በዓል ነው ሲሉ ገልጸውታል። 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ሕገ-መንግሥታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሠላም" በሚል መሪ ሃሳብ ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም