ለስፖርተኞች የሚሰጠውን ሽልማት ወጥነት ያለው ለማድረግ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

155
ኢዜአ ህዳር 28 /2012 አገር ወክለው ለሚወዳደሩ ስፖርተኞች የሚሰጥን ሽልማት አንድ ወጥ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 23ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል። በጉባዔው የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ቀደም ባለው ጊዜ አገርን ለሚወክሉ አትሌቶች የገንዘብና የመሬት ማበረታቻ ሽልማት ይሰጥ እንደነበር አንስታለች። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት በኩል የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ቢኖርም የመሬት ስጦታ ብዙም እንደማይሰጥ ተናግራለች። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ስፖርተኞች አገር ወክሎ የመወደዳር ፍላጎት ማጣት እያሳዩ ነው ብላለች። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ስፖርተኞች ከሚለፉት ልፋት አንጻር የሚሰጣቸው ሽልማት ዝቅትኛ ነው ብለዋል። በተለይ በግል ቢወዳደሩ ዳጎስ ያለ ሽልማት እንደሚያገኙ እየታወቀ አገርን አስቀድመው የሚወዳደሩና የአገርን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ስፖርተኞች በቂ ማበረታቻ እያገኙ አይደለም ነው ያሉት። ይህን ሁኔታ በማሻሻል ለአትሌቶች ሞራል መስጠትና ማበረታታት ይገባል ብለዋል። በጉዳዩ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በሰጡት ምላሽ መንግስት ለስፖርቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ገለጸዋል። አገር ወክለው ለሚወዳደሩ አትሌቶች መንግስት የማበረታቻ ሽልማት እየሰጠ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ይሁን እንጂ ሽልማቱ ወጥነት ባለው መልክ እየተሰጠ አለመሆኑን ጠቁመዋል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዋናነት የሽልማት አሰጣጡን የሚመለከት መመሪያ አለመኖሩ ነው ብለዋል። አሁን ላይ ይህን ችግር ለመፍታት አገርን ወክለው ለሚወዳደሩ አትሌቶች ሽልማት በምን መልኩ መስጠት እንደሚገባ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም