በኢትዮጵያ ሃቀኛ ፌዴራሊዝም እንዳይተገበር ያደረጉ መሰረታዊ ጉድለቶች ነበሩ

100
ኢዜአ ህዳር 27/2012 በኢትዮጵያ ሃቀኛ ፌዴራሊዝም እንዳይተገበር ያደረጉ መሰረታዊ ጉድለቶች እንደነበሩ የዓለም ዓቀፍ የህግ ምሁሩ ዶክተር ዮናስ ተስፋ ገለጹ። ኢዜአ በህገመንግስት ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ዶክተር ዮናስ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች አለመከበርና ለፍትህ መጓደል የዳረጉ ሁኔታ ነበር። በዚህ የተነሳም ለሶስት አስርታት በተዘረጋው ስርዓት ሃቀኛ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል። ለሁሉም የምትመች የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊት አገር የመገንባት ሂደቱ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል። አገሪቱ ሃቀኛ ፌዴራሊዝም እውን እንዳታደርግ እንቅፋት ሆነው የነበሩትን ጉዳዮች ዶክተር ዮናስ ገልጸዋል። በተለይም ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ያራምደው የነበረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም ቁልፍ ችግር እንደነበረ ተናግረዋል። ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄዎች ከህዝብ ጋር ሆኖ መፍታት አለመሞከሩና የፓርቲው አድራጊ ፈጣሪ መሆንና የሃሳብ ብዝሃነትን የማይቀበል መሆኑ ፌዴራሊዝም በትክክል እንዳይተገበር እንቅፋት መሆኑን አመልክተዋል። በህዝብ፣ በመንግስትና በፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባውን መሰረታዊና ተፈጥሯዊ ልዩነት የሚደመስስ መሆኑ ፌዴራሊዝም በስም እንጂ በተግባር እንዳይኖር ያደረገ መሆኑን ዶክተር ዮናስ አመልክተዋል። የውይይት መድረኩ ተሳታፊ የነበሩት ወይዘሮ ሃዋ አሊ በበኩላቸው ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳገኙ የሚገለጸው የተሳሳተ እንደሆነም ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም