ፓርቲው የክልሉ ህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ የጋምቤላ ክልል አመራሮች ገለጹ

106
ኢዜአ  ህዳር  27/2012 የብልጽግና ፓርቲ ቀደም ሲል የክልሉ ህዝብ ሲያቀርቧቸው የነበሩት እኩል የፖለቲካና የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን የጋምቤላ ክልል አመራሮች ገለጹ። በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም ዙሪያ የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ውይይት አካሄደዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ፓርቲው የክልሉ ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ እኩል የመወሰንና የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ሲያነሳቸው ለነበሩት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው። ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡጁሉ ኡቻላ በሰጡት አስተያየት የብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም የኢትየጵያ ህዝቦች እኩል የፖለተካና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስልል መሆኑን ተናግረዋል። ቀደም ሲል የነበረው ኢህአዴግ ጋምቤላን ጭምሮ አምስት ክልሎችን አጋር በማለት በሀገራቸው ፓለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የመወሰን መብት ነፍጓቸው መቆየቱን አስታውሰዋል። አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ቀደም ሲል የነበሩትን ችግሮች በማረም የክልሉን ብሎም ሌላውንም የኢትዮጵያ ህዝብ እኩል የመወሰንና የመጠቀም መብትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አመልክተዋል። "በፓርቲው የተቀመጡ ፕራግራሞች ሳይሸራረፉ በአግባቡ ተግባሪዊ ማድረግ ከተቻለ የሁሉንም ህዝብ ጥያቄ የሚመልስና የሚስተናገድ ነው "ሲሉ ገልጸዋል። ውህደቱ አህዳዊ ስርዓትን ለመፍጠር ነው የሚባለው አስተሳሰብ ከእውነት የራቀ የተሳሳተ መረጃ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌለው ተሳታፊ አመራር አቶ ማህበር ኮር ናቸው። አህዳዊ ስርዓት መባል ካለበት ባለፉት 27 ዓመታት ጋምቤላና ሌሎች ክልሎች አጋር በማለት በሀገራቸው ጉዳይ እንዳይወሰኑ አግሎ የቆየው ኢህአዴግ መሆኑን እንዳለበት ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪው እንደገለጹት የብልጽግና ፓርቲ አካታች፣አቃፊና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ልማትና ብልጽግና ለማሸጋገር የሚስችል ፓርቲ ነው። አቶ ቲቶ ሐዋርያ በበኩላቸው ከአሁን በፊት የነበረው የፖለቲካ ሂደት ችግር የነበረበት፣ በተለይም የጋምቤላና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን የበይ ተመልካች አድረጎ የቆየ መሆኑን ተናግረዋል። የብልጽግና ፓርቲን እነዚህን ችግሮች እንደሚፈታ ገልጸው " ጨፍላቂ ነው እያሉ የሚወሩ አካላት ጥቅማቸው የተነካበችውና በህዝቦች እኩልነት የማያምኑ አካላት ናችው" ብለዋል። የክልሉ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ተንኳይ ጆኮ  እንዳሉት ፓርቲው የሀገሪቱን እድገትና የጋራ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚስችል ነው። ፓርቲው አካታችና አቀፊ ከመሆኑም ባለፈ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም