ኢትዮጵያ ካላት የልማት ፍላጎት አኳያ የበለጠ የገንዘብ ድጋፍ ትፈልጋለች---ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

111
ኢዜአ ህዳር 27/2012 ኢትዮጵያ ካላት የልማት ፍላጎት አኳያ የአውሮፓ ህብረት እስካሁን እያደረገ ካለው ድጋፍ የበለጠ እንደምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙትን ሚስ ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዝዳንቷ ቀዳሚ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ማድረጋቸውን አድንቀው፤ ሕብረቱ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት አጋር መሆኑን አስታውሰዋል። ህብረቱ ባለፉት 40 ዓመታት የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆኖ መቆየቱንና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድጋፉ እየጨመረ መምጣቱንም ጠቅሰዋል። ይሁንና አገሪቱ ካላት የልማት ፍላጎት አኳያ ከህብረቱ የበለጠ የገንዘብ ድጋፍ እንደምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሸሸጉም። የአውሮፓ ሕብረት ከአፍሪካ ጋር በትብብር ለመስራት ትክክለኛ ውሳኔ መወሰኑንም አረጋግጠዋል። ሕዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም ኮሚሽኑን ለመምራት ከተሾሙ በኋላ ቀዳሚ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉት ፕሬዝዳንቷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮ-ኤርትራ ሰላም መምጣት የተጫወቱትን ሚና አድንቀዋል። የ2019 የሰላም የኖቤል አሸናፊ በሆናቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት ለቅኝ ግዛት ሳትንበረከክ ሉዓላዊቷን አስጠብቃ መቆየቷን አድንቀው፤ በአሁኑ ወቅት የጀመረችውን አገራዊ ለውጥም ለመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል። ፕሬዝዳንቷ ህብረቱ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም