ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ተደረገላት

65
ኢዜአ ህዳር 27/2012 የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛውን የገንዘብ ድጋፍ አደረገ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል የ170 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል። የድጋፍ ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና በህብረቱ የዓለምአቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ አፓርቪሊኔን ናቸው። ኮሚሽኑ በአንድ ጊዜ ይህን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ የመጀመሪያው ሲሆን ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዝ በስምምነቱ ጊዜ ተገልጿል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ ከህብረቱ ጋር ከጥቂት ዓመታት በፊት ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጓን አንስተዋል። በተለይም በሰላምና ጸጥታ፣ ሽብርተኝነትን በጋራ መከላከል፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። ኢትዮጰያ ከራሷ አልፋ በአፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣትና ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር በምታደርገው ጥረት ህብረቱ ሲደግፋት እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ በአንድ ጊዜ ይህን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ግን የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያን መደገፍና በአገሪቱ መዋዕለ-ነዋይን ስራ ላይ ማዋል ለቀጣናው ያለውን ጠቀሜታ ያብራሩት ሚኒስትሩ አገሪቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ኃላፊነቷን እየተወጣች ነው ብለዋል። የገንዘብ ድጋፉ አገሪቱ ለጀመረችው የለውጥ ስራ አጋዥ ከመሆን ባለፈ ከአውሮፓ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር እንደሆነም አንስተዋል። የህብረቱ የዓለምአቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ አፓርቪሊኔን በበኩላቸው ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። የ170 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፉም ኢትዮጵያ እያሳየችው ያለውን ለውጥ ለማበረታታት የተደረገ ነው ብለዋል። ከድጋፉ 100 ሚሊዮን ዩሮው ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ 50 ሚሊዮን ዩሮ ለጤናው ዘርፍ ማሻሻያ፣ 10 ሚሊዮን ዩሮ ለምርጫ ቦርድ አቅም ግንባታ፣ ቀሪው 10 ሚሊዮን ዮሮ ደግሞ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለኢንቨስትመንት ማሻሻያ እንደሚውል ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም