ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ሴቶችን መሪ በማድረግ ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ ናቸው---ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

69
ኢዜአ ህዳር 27/2012 ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የሴቶችን መሪነት በማረጋገጥ ስኬታማ መስመር ላይ የገቡበት ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ ናቸው ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። ፕሬዝዳንቷ የመጀመሪያዋን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ሴት ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይንን በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ሁለቱ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ከህብረቱ ጋር ስለነበራትና ቀጣይ ስለሚኖሩ የግንኙነት አቅጣጫዎች የመከሩ ሲሆን በተለይም ሴቶችን በማብቃት ረገድ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ "ኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ መሪነት በማብቃት ትልቅ ለውጥ ባመጣችበት ተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የአውሮፓ ህብረትም የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዝዳንት መምረጡ አስደስቶኛል" ብለዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በሚኖራት ግንኙነት በመካከላቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶችን ማብቃትና ወደ ኃላፊነት ማምጣት አንዱ ተግባራችን ይሆናል ብለዋል። ሚስ ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ሴቶችን በማብቃት ያላቸውን ልምድ አድንቀው በቀጣይ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ህብረቱ ሴቶችን ወደ ኃላፊነት ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም