ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት እንሰራለን-ኢዜማ

53
ኢዜአ ህዳር 27/ 2012 እየተፈጠረ ያለውን ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ በመጠቀም የሀገር ሰላምና የህዝቦች አንድነት እንዲከበር በትጋት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊና ፍትህ ፓርቲ አስታወቀ፡፡ ፓርቲው በድርጅቱ ፕሮግራምና አደረጃጀት ዙሪያ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በወቅቱ እንደገለጹት ፓርቲው በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና የህዝቡ ጥቅም  እንዲጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት፣ በህዝቡ ዘንድ አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር አበክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ። ለህዝቦች አንድነትና ለሀገር ሰላም መጠናከር  ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል ። የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በየአካባቢያቸው ያለውን ሰላም በማስጠበቅ በኩል በትኩረት እንዲሰሩ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል ። የፓርቲው የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ኡኬሎ አኳይ በበኩላቸው በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ አሁን በተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በነጻነት መንቀሳቀስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እድሉን በመጠቀም ለክልሉ ህዝብ ሰላምና ጥቅም ሊሰሩ እንደሚገባ  አስገንዘበዋል፡፡ “በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ሁሉም እኩል ተሳታፊ እንዲሆንና ያለውን ሀሳብ በመያዝ ለሀገር አንድነት እንዲሰራ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል” ያሉት ደግሞ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ኡቻን ኡገቱ ናቸው። የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ጨምሮ ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም፣ ለህዝቦች አንድነትና አብሮነት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅረበዋል ። በውይይት መድረኩ በፓርቲው ፕሮግራምና አደረጃጀት ዙሪያ ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች በኢዜማ አመራሮቹ ምላሽ ተሰጥቷል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም