የኢትዮጵያና የህንድ ስራ ፈጣሪዎች ትስስርን ማጠናከር አላማ ያደረገ ፕሮግራም የፊታችን ሰኞ በአዲስ አበባ ይጀመራል

91
ኢዜአ ህዳር 27/2012 በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ መስኮች የኢትዮጵያና የህንድ የስራ ፈጣሪዎች ግንኙነት ማጠናከርና የገበያ ትስስር መፍጠርን አላማ ያደረገው የኢትዮ-ህንድ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ገበያ ልማት ትስስር ፕሮግራም ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀመራል። በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ከህዳር 29  እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄደው ፕሮግራም ሚኒስቴሩ እና የህንዱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ገበያ ልማት ፕሮግራም በጋራ ያዘጋጁት ነው። በፕሮግራሙ ላይ የ31 የህንድ እና የ62 ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች የተዘጋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚታዩበት ሲሆን፤ የህንድ እና ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ውጤት የሚታይበት እንዲሁም የኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ ምርት ውጤቶች አቅማቸውን የሚገነቡበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚዲያና ፕሬስ ዳይሬክተር ተስፋዬ አለምነው ለኢዜአ እንደገለጹት በፕሮግራሙ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን መስኮች ከህንድ የመጡ የስራ ፈጣሪዎች ያላቸውን ስራ በማቅረብ ልምዳቸውን ለኢትዮጵያ የስራ ፈጣሪዎች ያቀርባሉ። በፕሮግራሙ ላይ የሚሳተፉት 31 የህንድ የስራ ፈጣሪዎች ከ1 ሺህ 500 በላይ በህንድ ከሚገኙ የስራ ፈጣሪዎች ተወዳድረው የተሻለና ውጤታማ በመሆናቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ያሉ የስራ ፈጣሪዎች ስራ ከመሸለምና እውቅና ከመስጠት ባለፈ ወደ ገበያው ገብተው የመስራት ልምዱ እንደሌለም ተናግረዋል። በዚህ ረገድ የህንድ የስራ ፈጣሪዎች ያላቸውን ተሞክሮ የሚያቀርቡ ሲሆን ይሄም ለኢትዮጵያውያን የስራ ፈጣሪዎች ትልቅ ልምድ ማግኛ እንደሆነ ገልጸዋል። በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ስራ መፍጠር ላይ ትልቅ ስም ካላቸው አገራት አንዷ ህንድ እንደሆነች ገልጸው፤ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ የስራ ፈጠራም የዳበረ ልምድ እንዳላት ጠቅሰዋል። በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን መስኮች የህንድ የስራ ፈጣሪዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ ስራ ፈጣሪዎች ጋር በሽርክና የሚሰሩበትን ምቹ መደላድል ለመፍጠርም አገራቱ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበርም ነው አቶ ተስፋዬ ያስረዱት። የኢትዮ-ህንድ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ገበያ ልማት ትስስር ፕሮግራም የሁለቱ አገራት የስራ ፈጣሪዎች በሽርክና የሚሰሩበት ሁኔታንም የሚያመቻች ነው ብለዋል። በእርሻና ምግብ ማቀነባበር፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በውሃ እና የውሃ ንጽህና፣ በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት እንዲሁም በሌሎች ተመሳሳይ ዘርፎች ላይ የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎች ለፕሮግራሙ ተለይተዋል። ፕሮግራሙ ውጤታማ የሆኑ የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪዎች ለውጭ አገራት ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡበትን እድል መፍጠርና ከሌሎች ሀገራት ጋር የመስራት ልምድንም እንዲቀስሙ ማድረግ፣ በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ጥምር የኢኖቬሽን የስራ ውጤቶች የሚቀርቡበት ኤክስፖ ማዘጋጀት፣ አዳዲስ የአሰራር ዘይቤዎች እና የፈጠራ ስራዎች የሚበለጽጉበት እና ስራ ፈጣሪዎች ስራዎቻቸውን ወደ ገበያ የሚያቀርቡበትን መደላድል በማዘጋጀት የስራ ዕድልና ሀብትን መፍጠር የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ያለመ ተግባር መሆኑን አክለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም