በምስራቅ ወለጋ ዞን 1ሺህ 678 ሔክታር መሬት ከተምች ነፃ ተደረገ

60
ነቀምቴ ሰኔ 15/2010 በምሥራቅ ወለጋ ዞን የተከሰተውን የተምች ወረርሽኝ ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ1 ሺህ 678 ሄክታር  መሬት ከተምች ነፃ ማድረግ እንደተቻለ የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘውዴ መኮንን ለኢዜአ እንዳስታወቁት  ተምቹ በዞኑ 12 ወረዳዎች በሚገኙ 110 ቀበሌዎች በ2 ሺህ 854 ሄክታር መሬት ላይ ተከስቷል፡፡ እስከ አሁን በተካሄደው የመከላከል ስራ 1ሺህ 678 ሔክታር መሬት ከተምች ነፃ ማድረግ ተችሏል ። በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ በተካሄደው የመከላከል ስራ ላይ  6 ሺህ 210 አርሶ አደሮች  የተሳተፉ ሲሆን 261 ሊትር ኬሚካል ለወረዳዎቹ ተከፋፍሎ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ በኬሚካል እጥረት ምክንያት ተምቹ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የኦሮሚያ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ተጨማሪ ኬሚካል እንዲልክ ተጠይቆ ፈቃደኝነቱን መግለፁን ተናግረዋል ። የተምቹን ስርጭት ለመቆጣጠር በዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሚመራ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡ በመከላከል ስራው ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል  በኤባንቱ ወረዳ የቡርቃ ጉዲና ቀበሌ አርሶ አደር ኦልጅራ ኤጀታ በሰጡት አስተያየት በመጋቢት ወር የጣለውን ዝናብ በመጠቀም በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በዘሩት በቆሎ ላይ ጉዳት  ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ ተምቹን በኬሚካልና በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የቀቀሮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ነሞ አልተታ በበኩላቸው  በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የዘሩት የበቆሎ ቡቃያ  በተምች በመወረሩ በባህላዊና በኬሚካል ርጭት በመከላከል ሰብሉን ከጉዳት መታደጋቸውን ተናግረዋል ። አርሶ አደር አብዲሣ ደበሎ እንዳሉት ደግሞ  በማሳቸው ላይ አልፎ አልፎ የሚታየው ተምች ስርጭቱ እንዳይስፋፋ ከአከባቢው አርሶ አደር ጋር በመሆን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም