የመከላከያ ሰራዊት ከፖለቲካ ድርጅቶች ነጻና ገለልተኛ በመሆን ውግንናውን ከህዝብ ጋር ማድረግ አለበት

132
ህዳር 26/2012   በመከላከያ ሰራዊት እየተተገበረ ያለውን ሪፎርም ተከትሎ የሰራዊቱን መተዳደሪያ ደንብ በማሻሻል የሰራዊቱን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል። የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት  አዲስ በተሻሻለው የመከላከያ ሰራዊት መተዳደሪያ ደንብና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለሰራዊቱ የሰጠው ስልጠና መጠናቀቁን ባደረሰን መግለጫ አስታውቋል። በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ኢታማጆር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ "ሰራዊቱ ከፖለቲካ ድርጅቶች ነጻና ገለልተኛ በመሆን ውግንናውን ከህዝብ ጋር ማድረግ አለበት" ብለዋል ። የአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎም  የሠራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት የሰራዊቱን ግንባታና የግዳጅ አፈፃፀሙን ይበልጥ ለማሳደግ ታልሞ ነው ብለዋል። በዚህም ሰራዊቱንና ቤተሰቡን እንዲሁም ሲቪል ሰራተኛውን ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። የተጀመረውን ተቋማዊ ለውጥ ለማሰቀጠልና የዘመናዊ ሠራዊቱን ዝግጁነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም ጄነራል ብርሃኑ አስታውቀዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም