በጋሞ ጎፋ ዞን ዞናዊ የተማሪዎች ፈተና እየተሰጠ ነው

99
አርባ ምንጭ ሰኔ 15/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን የዘንድሮ የ4ኛ ክፍል ዞናዊ ፈተና እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ ብሔራዊ ፈተናዎች ኮማንድ ፖስት ገለጸ። የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ አቶ ማሄ ቦዳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፈተናው ከትናንት ጀምሮ እየተሰጠ ያለው በዞኑ በ72 ክላስተሮች በተዘጋጁ 794 የፈተና ጣቢያዎች ነው። ዞናዊ ፈተናው በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ በጋሞ ጎፋ ዞን ብቻ የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ፈተናው በአፍ መፍቻ ቋንቋ የተማሩ ሕጻናት የመጻፍ፣ የማንበብና ማስላት ችሎታቸውን ወጥ በሆነ መንገድ የመመዘን ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል። በ2004 ዓ.ም ለሙከራ የተጀመረው ዞናዊ ፈተና ከታቀደለት ዓላማ አንጻር ስኬተማ መሆኑን የገለጹት አቶ ማሄ፣ ዘንድሮ ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን በሰላማዊ ሁኔታ በመፈተን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በአምስት የትምህርት ዓይነቶች እየተሰጠ ላለው ፈተና 160 የፈተና አስተባባሪዎች መሰማራታቸውንም አቶ ማሄ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም