ኬንያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ገለጸች

68
ኢዜአ ህዳር 27/2012 ኬንያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ የኬንያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር አሚና ሞሐመድ ገለጹ። የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት ኤልዶሬት ከተማ ዓመታዊ ስብሰባውን አድርጓል። በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በሁለቱ አገራት አትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር በጉጉት የሚጠበቅ እንደሆነም ተናግረዋል። ይኸን ፉክክር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሰደግ እንዲረዳም ሁለቱ አገሮች በልምድ ልውውጥና በስፖርት ተቋማት ግንባታ እንዲደጋገፉ ሚኒስትሯ ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የሁለቱም አገሮች አትሌቶች ከአበረታች ቅመሞች ራሳቸውን እንዲጠብቁና ዘርፉ የተጋረጠበትን አደጋ ለመፍታት ተባብረው በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ዶክተር አሚና ገልጸዋል። በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በስብሰባው ተገኝተው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን መልዕክትን አቅርበዋል። አምባሳደሩ እንዳሉት በኢትዮጵያና በኬንያ አትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር በዓለም የአትሌቲክስ መንደር ተወዳጅና ተናፋቂ ከመሆኑም በላይ የውድድሮቹ ማድመቂያም ነው። ስፖርት ህዝብ ለህዝብ ትስስርና ለአንድነት ያለውን ጠቀሜታ ያወሱት አምባሳደሩ፤ በዚህም ሁለቱ አገሮች በጋራ እንደሚሰሩም ማስታወቃቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም