የአፍሪካ ልማት ባንክ ለሰቆጣ ቃል ኪዳን ስርፃተ ምግብ ማሻሻያ 38 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

54
ኢዜአ ህዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም.. የአፍሪካ ልማት ባንክ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት የሚካሄደውን የስርዓተ ምግብ ማሻሻል ፕሮግራም 38 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግስት በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በአማራና በትግራይ የሚስተዋሉ የስርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመቅረፍ የ15 ዓመት ፕሮግራም ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን የሰቆጣ ቃል ኪዳን የፌደራል ፕሮግራም አስታውቋል። የባንኩ ልዑካን ቡድን ከፌደራልና ከአማራ ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በፕሮግራሙ አተገባበር ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በባህርዳር ከተማ እያካሄደ ይገኛል ። በባንኩ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ  ዶክተር አብዱል ካማራ እንዳሉት ባንኩ የአፍሪካ ሃገራት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እድገት እንዲያስመዘግቡ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ። በአሁኑ ወቅትም ባንኩ 38 ሚሊየን ዶላር በመመደብ በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት አማካኝነት በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የስርዓተ ምግብ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል። በውሃ ተቋማትና በመስኖ ግንባታ፣ በጤና፣ በትምህርትና በስርዓተ ምግብ ማሻሻያ ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ከስርዓተ ምግብ እጥረት  ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጤናና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ ድጋፍ ነው ብለዋል። ከስድስት ባልበለጡ ወረዳዎችና በአነስተኛ ፕሮግራሞች በመጀመር በቀጣይ የተገኘውን ውጤትና ተሞክሮ በመቀመር ወደ ሌሎች ወረዳዎች ለማስፋት በሚያስችል መልኩ ፕሮግራሙ እንዲተገበር ባንኩ አቅጣጫ ማስቀመጡን አመልክተዋል። በሰቆጣ ቃል ኪዳን የፌደራል ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ክፍል ከፍተኛ የፕሮግራም ማኔጀር ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ በበኩላቸው የቃል ኪዳን ስምምነቱ በአማራና በትግራይ ክልሎች የተከዜ ተፋሰስን መሰረት ተደርጎ የሚተገበር የመንግስት ፕሮግራም ነው። በዚህም በያዝነው ዓመት በቃል ኪዳኑ የሚተገበሩ ፕሮግራሞችን ለማስፈጸም 477 ሚሊየን ብር የፌደራል መንግስት በመመደብ ስራውን ያስጀመረ ሲሆን የክልል መንግስታትም የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ በመመደብ እየተንቀሳቀሱ ነው። ይሁን እንጂ በአካባቢው ካለው የልማት ፍላጎትና ከችግሩ ስር ስፋት አንጻር ሲታይ በመንግስት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ሌሎች ረጂ ድርጅቶችን በማስተባባር ሃብት የማምጣት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናገረዋል። በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ልማት ባንክ ገንዘብ በመመደብ በተጠኑ ወረዳዎች የተለያዩ የልማት ስራዎችና የማህበራዊ ደህንነት ፕሮግራሞችን ለመተግበር የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው የጋራ ውይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል ብለዋል። ከሚካሄዱ የጤና፣ የትምህርት፣ የውሃና መስኖ ፕሮግራሞች ባሻገር የስርዓተ ምግብን ለማሻሻል እንዲችል በአርሶ አደሮች ማስልጠኛ ጣቢያዎች የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት የሚያስችል የአመራረት ዘይቤን በመተግበር ማህበረሰቡን ለማስተማር ይሰራል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ለሰቆጣ ቃል ኪዳን የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የኤፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮነን ከመሰረተ ልማት ባሻገር በሰው አእምሮና ጤና ላይ መስራት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰው ለባንኩ ፕሬዚዳንት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑን አስረድተዋል። በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካሪ አቶ አለሙ ጀምበር እንዳሉት  የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በክልሉ በሚገኙ ሰሜን፣ ማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ በሰሜን ወሎና ዋግ ህምራ ዞኖች እየተተገበረ የሚገኝ ነው። በእነዚህ ዞኖች በሚገኙ 27 ወረዳዎች ከስርዓተ ምግብ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የፌደራል መንግስትና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ከሚመድቡት ሃብት ባሻገር ክልሉ ከ343 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ መመደቡን ተናግረዋል። ፕሮግራሙ የዞኖቹን ህዝብና የቀጠናውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማፋጠን እንደሚያስችል ክልሉ በማመኑ ከሁሉም አስቀድሞ ባለፈው ዓመት 575 ሚሊየን ብር በመመደብ ወደ ስራ መግባቱን አውስተዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ የፌደራል መንግስትና የአፍሪካ ልማት ባንክ ሀብት መድበው ወደ ስራ መግባታቸው በአካባቢው የሚስተዋለውን ድህነትና ኋላ ቀርነት ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም