ህብረተሰቡ ቁጠባን ባህሉ ማድረግ አለበት - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

53

ኢዜአ ህዳር 26 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ9ኛ ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ ፕሮግራሙን ታህሳስ 22 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀምር አስታወቀ።

ባንኩ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙና በይቆጥቡ ይሸለሙ  መርሃ ግብር  ለባዕድለኞች በርካታ ሽልማቶች ማበርከቱ ይታወቃል።

ቁጠባ ነገን በማሰብ  ከገቢ ላይ በተወሰነ መጠን በመቀነስ የሚቀመጥና ለኢንቨስትመንት መነሻ  በመሆን ራስንና ቤተሰብን እንዲሁም አገርን የሚጠቅም ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደንት አቶ ባጫ ጊና የ9ኛ ዙር የይቆጥቡ ይሸልሙ  መርሃ ግብር  አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ "ቁጠባ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና፤ ማህበራዊ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

ለአገር ኢኮኖሚ እድገትም ቁልፍ በመሆኑም ማህበረሰቡ ቁጠባን  ባህሉ በማድረግ ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ባንኩ ለግሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍና ለሀገራዊ  የልማት ስራዎች ፋይናንስን በተሟላ  ሁኔታ ለማቅረብ ቁጠባን የሚያበረታቱ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጃት  አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውሰዋል።

የ9ኛው ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር ካለፉት  ስምንት ዙሮች የተሻለና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ሽልማቶችን ይዟል።

በዚህም 2 መኖሪያ ቤት፣ 3 መለስተኛ የጭነት መኪናዎች፣ 15 ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢልና ሌሎችም በሽልማቱ ተካተዋል።

ይህንን የማትጊያ  መርሃ ግብር  በተገቢው ሁኔታ  ለህብረተሰቡ በማድረስ  የቁጠባ ባህልን ለማሻሻል ሚዲያ ጉልህ ድርሻ ስላለው የባንኩን ተግባር በማስተዋወቅ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የዘጠነኛው ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ  ግብር  ከታህሳስ  ወር መጨረሻ  እስከ  ስኔ 23 ቀን  2012 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ መሆኑን በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም