በገበያ ትስስር አጦት የሸንኮራ ምርታችን ተገቢውን ዋጋ እያገኘን አይደለም- የባህር ዳር ዙርያ አርሶ በአደሮች

92
ህዳር 26 ቀን 2012 በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ በሸንኮራ አገዳ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች በገበያ ትስስር እጦት ምክንያት ለምርታቸው ተገቢውን ዋጋ እያገኙ አለመሆናቸውን ገለፁ። የወረዳው ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ አርሶ አደሮቹ በሚፈጠርላቸው የገበያ ትስሰር ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው አስታውቋል። በልማቱ ከተሰማሩ መካከል አርሶ አደር  ብርሃኑ ታደገ ለኢትዮጰያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በአንድ ሄክታር ከግማሽ መሬት ላይ ለሚያለሙት ሸንኮራ አገዳ በአመት 30 ሺህ ብር ወጭ ያደርጋሉ። በአመት ከሚሰበስቡት ምርት ሽያጭ 120 ሺህ ብርና ከዛ በላይ ገቢ ማግኘት ሲገባቸው እያገኙ ያለው ግን ከ70 ሺህ ብር በልጦ እንደማያውቅ ተናግረዋል። "በባህር ዳር ከተማ የመሸጫ ቦታ እንዲመቻችልን ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ሊፈቀድልን ባለመቻሉ በደላላ አማካኝነት  ምርታችንን  በቁሙ ከመሬችን ላይ ለነጋዴዎች ለማስረከብ በመገደዳችን ለኪሳራ እየተዳረግን ነው" ብለዋል ። ልማቱን በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ እያካሄዱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  አርሶ አደር ደርሶ ሊቁ ናቸው። "ለፍተንና ደክመን የምናመርተውን ሸንኮራ በህገ-ወጥ ደላላ መልካም ፈቃድ ላይ ተወስነን ስለምንሸጥ ለኪሳራ ተዳርገናል" ብለዋል። ባለፈው አመት 80 ሺህ ብር ሊያወጣ የሚችል ሸንኮራ በደላሎች ጫና 60 ሺህ ብር ለመሸጥ ተገደው እንደነበር አስታውሰዋል ። መንግስት የገበያ ትስስር ካልፈጠረላቸው ዘንድሮም ተመሳሳይ እድል እንደሚጠብቃቸው አርሶ አደሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የወረዳው ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ  አገሬ ጌታሁን  ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ አርሶ አደሮቹ በተደጋጋሚ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ፍቃደኛ ባለመሆን ሳይጠቀሙበት መቅረታቸውን ተናግረዋል። "ለዚህም ምክንያቱ አልሚዎቹ ከህገ-ወጥ ደላሎች ጋር ትስስር ስላላቸውና በተለይም ደላሎቹ ልጆቻቸው በመሆናቸው እንዲጠቀሙላቸው በመፈለጋቸው ነው" ብለዋል። በተለይም በርካታ ህገወጥ ደላሎች በሚገኙበት አንዳሳ ቀበሌ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ደብረ ማርቆስና ጎንደር ለሚገኙ ነጋዴዎች እንዲያስረክቡ የገበያ ትስስር ቢፈጠርላቸውም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። እንደ ወይዘሮ አገሬ ገለጻ አርሶ አደሮቹ ለሚያሰሙት ጥያቄ ተገዥ ከሆኑ የገበያ ትስስር ይፈጠርላቸዋል ። በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ  500 የሚሆኑ አርሶ አደሮች በ241 ሄክታር መሬት ላይ በሸንኮራ አገዳ ልማት መሰማራታቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም