ኢትዮጵያ ከትምህርት ገበታ ውጭ ለሆኑ ሕፃናት የሚውል 27 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች

74
ህዳር 26/2012 ኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ለተፈናቀሉ 750 ሺህ ህጻናትን ለማስተማር የሚያግዝ የ27 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች። ድጋፉን ያደረገው 'ትምህርት አይጠብቅም' የተሰኘ ዓለም አቀፍ ፈንድ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ገልጿል። ለሶስት ዓመት የሚቆየው ይህ መርሃ ግብር 161 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል ተብሏል። የተገኘው የ27 ሚሊዮን ድጋፍ በመርሃ ግብሩ በኩል በግጭት ምክንያት ትምህርት ላቋረጡ 750 ሺህ ህጻናት ትምህርት ለማዳረስ የሚውል ነው። ድጋፉ ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን በዘላቂነት  ለመፍታት  አዲስ ለነደፈው መርሃ ግብር ትግበራም ይውላል ተብሏል። ይህ ድጋፍ በዓለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት በኩል ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ድጋፉ ኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ህጻናትና ወጣቶችን ለማገዝ እንደሚረዳ ገለጸዋል። ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዘላቂነት ምላሽ የሚሰጥ መርሃ ግብር በመዘርጋት የወደፊት አገር ተረካቢ ህጻናት ላይ መዋዕለ ነዋያችንን እናፈሳለንም ብለዋል። ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት የተነደፈውን መርሃ ግብር ትምህርት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ከሴቭ ዘ ችልድረንና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ጋር የሚተገብረው ነው። መርሃ ግብሩ ዕድሜያቸው ለትህምርት የደረሱ ህጻናት አካታችና ጥራት ያለው የትምህርት እድል እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል። በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ውጭ እንደሆኑ በመረጃው ተመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም