የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የአርሶ አደርን ሰብል በመሰብሳብ ድጋፍ እያዳረጉ ነው

58
ኢዜአ  ህዳር 26/2012 የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች  የአርሶ አደሩን ሰብል በመሰብሰብ ድጋፍ እየዳረጉ ነው። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ለአርሶ አደሩ ድጋፍ እያደረጉ ያሉት በምስራቅ ወለጋ ዋዩ ቱቃ እና ስቡ ስሬ ወረዳዎች ውስጥ በመሰማራት መሆኑን ዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር በሻቱ ፈረደ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት ተማሪዎችና መምህራን ጨምሮ አንድ ሺህ 500 የሚጠጉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ትናንት በወረዳዎቹ ለአርሶ አደሩ ድጋፍ አድርገዋል። የአርሶ አደሩ ምርት ወቅቱን ባልጠበቀው ዝናብ እንዳይበላሽ አጭዶ በመሰብሰብ የሚሰጡት ድጋፍ እንደሚቀጥልም ዶክተር በሻቱ አስታውቀዋል። በዩኒቨርሲቲው የሕዝብ አስተዳደርና የልማት አመራር የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ዳዊት ነገራ በሰጠው አስተያየት የአካባቢውን አርሶ አደሮች ማገዛቸው አንዱ ለአንዱ በማሰብ የነበረው የመደጋገፍና የመረዳዳት አኩሪ ባህል እንደሚያጎለብት ገልጿል። በአካውንቲንግ የሶሰተኛ ዓመት ተማሪ ዮሐንስ ሁንዱማ በበኩሉ "የሰብል አሰባሰብ ዘመቻው የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ነው "ብሏል። የስቡ ስሬ ወረዳ አርሶ አደር ኑርቱ ደረሳ በሰጡት አስተያየት የደረሰ ሰብላቸው ወቅቱ ባልጠበቀው ዝናብ እንዳይበላሽ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ባደረፈገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል። በመኸሩ ወቅት በወረዳው በተለያየ ሰብል ከለማው 40 ሺህ 26 ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ከ20ሺህ ሄክታር በላይ መሰብሰቡን የወረዳው ግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽ.ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ሙለታ ገልጸዋል። የደረሰ ሰብል በመሰብሰቡ ሂደት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት በመሳተፍ ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። በተመሳሳይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉድሩ ወረዳ የደረሰ ሰብል በዘመቻ እየተሰበሰበ ነው። የወረዳው የእርሻ የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ አብዲሣ ለኢዜአ እንደገለጹት በሰብል አሰባሰቡ ስራ በአከባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለአንድ ሳምንት በመዝጋት ተማሪዎችና መምህራን ተሳትፈዋል። የፖሊስ አባላትና ሌሎችም የመንግሥት ሠራተኞች ድጋፍ አድርገዋል። በወረዳው በምርት ዘመኑ በተለያየ የሰብል ዘር ከተሸፈነው 35ሺህ460 ሄክታር መሬት በአንድ ሳምንት ዘመቻ 19ሺህ 857 ሄክታር መሬት ላይ ደርሶ የነበረ ሰብል መሰብሰቡን ኃላፊው አስረድተዋል። የወረዳው ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኪሲ በላይ በበኩላቸው የደረሰ ሰብል በመሰብሰቡ ስራ ከ25ሺህ በላይ ተማሪዎችና መምህራን መሳተፋቸውን ተናግረዋል ፡፡ በስራ ዘመቻው በአንድ ሄክታር የነበራቸውን የጤፍ ምርት አጭዶ በመሰብሰብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው የገለጹት ደግሞ በወረዳው የቀነኒ ቀበሌ አርሶ አደር ገልገሎ ኢተፋ ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም