አስተዳደሩ ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተሳትፎውን ማሳደግ አለበት ---የድሬዳዋ ወጣቶች

65
ህዳር 26/2012 የድሬዳዋ አስተዳደር ሥር ለሰደደው የወጣቶች የሥራ ጥያቄ ልዩ ትኩረት በመስጠት ትርጉም ያለው ሥራ መስራት እንዳለበት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለፁ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ ለሁለት ወራት በተካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተሳተፉ ወጣቶች የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የምስጋና ሥነ ሥርዓት ዛሬ አዘጋጅቷል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የተሣተፉና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች እንደተናገሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለወጣቱ እየሰጠ የሚገኘው ትኩረት ሊበረታታ የሚገባው ቢሆንም ካለው የወጣቱ ችግር ስፋት አኳያ የተቀናጀ ሥራ ሊሰራ ይገባል፡፡ ወጣት ሰላሀዲን አሊ በሰጠው አስተያየት ወጣቱ ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የልማት ሥራዎች እንደተሳተፈው ሁሉ የአካባቢው ሰላምና ልማት ለመጠበቅም ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ''በዚህ ዓመት የታየው ሁከትና ብጥብጥ አንዱ ምክንያት ሥራ እጥነት በመሆኑ አስተዳደሩ ለወጣቱ ችግሮች ልዩ ትኩረት በመስጠት ትርጉም ያለው ሥራ መስራት አለበት'' ብሏል፡፡ ወጣት ናርዶስ ጌታሁን አስተዳደሩ ወጣቱን ችግር ባጋጠው ጊዜ ብቻ ሣይሆን ሁልግዜም ወደታች ወርዶ ማወያየት ይገባዋል ብላለች፡፡ በድሬዳዋ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የመንግስት አካላት በተቀናጀ መንገድ በመስራት ለወጣቱ የሥራ እድል መፍጠር እንዳለበት አሳስባለች፡፡ ''መገለጫችን አንድነትና ፍቅር ነበር፤ የራሳቸውን አጀንዳ ፍላጎት የሚያራምዱ አካላት በፈጠሩት ችግር የወጣቱን ህብረት እያደፈረሱት ነው'' ያለው ደግሞ ወጣት አሚር መሐመድ ነው፡፡ ''የምንጠይቀው የሥራ እድል፤ የምንጠይቀው ተሣትፎና ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ለዚህ ሰላም መጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብረን እንሰራለን'' ብሏል፡፡ በኢንጂነሪንግ ሙያ የተመረቀው ወጣት ኢዩኤል አበበ በበኩሉ በተደጋጋሚ ጊዜ በስራ እጥነት በመመዝገብም ሆነ ከእኩዮቹ ጋር በመሆን ሥራ ለመፍጠር ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ተናግሯል፡፡ አስተዳደሩ ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግራቸውን በመፍታት ከብክነት ሊያድናቸው እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡ ወጣት ከሪማ ሐሰን በበኩሏ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታየው ለውጥ ወደ ድሬዳዋ መምጣት እንዳለበት ተናግራለች፡፡ ወጣቱ ህብረቱንና አንድነቱን በማጠናከር አሁን እየታየ የሚገኘው ሰላም ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን ገልጻለች፡፡ በምስጋናው ሥነሥርዓት ላይ የተሣተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፉአድ ከድር እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ አስተዳደሩ ለወጣቱ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሄ  ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወጣቱ ለድሬዳዋ ዕድገትና ሰላም ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል›› ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ ህዳር 11 ቀን 2012 ባደረገው ስብሰባ በመንግስት መዋቅርውስጥ ያሉ ክፍት የሥራ መደቦች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ያለሥራ ለተቀመጡ  ወጣቶች በዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ እስከ ፕሣ 5 ድረስ  እንዲቀጠሩ ወስኗል፡፡ በድሬዳዋ በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ እስከ 440 ክፍት የሥራ መደቦች መኖራቸውን ኢዜአ ባደረገው ቅኝት አረጋግጧል፡፡በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ 51 ሺ የድሬዳዋ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት የልማት ሥራዎች ማከናወናቸው ታውቋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም