ስምምነቱ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተገለፀ

50
ህዳር 25/2012 ኢዜአ በኢህአዴግና በአጋር ድርጅቶች መካካል ሰሞኑን የተደረሰው ስምምነት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ የህዝቦችን አንድነት እንደሚያጠናክር በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ብዙሃን ማህበራትና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ ። በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ማህበራት ለኢዜአ እንደገለጹት በፓርቲዎቹ መካካል የተደረሰው ስምምነት በአገሪቱ ዴሞክራሲንና ሰላምን በማስፈን ዜጎች እርስ በእርስ እንዲደማመጡና እንዲግባቡ ሰፊ እድል ይፈጥራል፡፡ የዞኑ አርሶ አደሮች ማህበር ሰብሳቢ አቶ መከተ ደባልቄ  እንደገለፁት የፖለቲካ ድርጅቶቹ የደረሱበት ስምምነት አገሪቱን ወደ ተሻለ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ የሚያሸጋግር ነው፡፡ ፓርቲዎቹ በወረቀት ስምምነት መፍጠር ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ህግና ደንብ ተከትለው ስምምነቱን ለዜጎች ጥቅም በሚበጅ መልኩ ለፍፃሜ ሊያበቁት እንደሚገባም ተናግረዋል  ። የዞኑ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ይርገዱ አያሌው በበኩላቸው ስምምነቱ ሃገራዊ አንድነትና መግባባት በመፍጠር ከድህነት ለመላቀቅ ያግዛል ብለዋል ። በተለይ 'እኔን ብቻ ሰሙኝ' ከሚል ኋላቀር አስተሳሰብ በመላቀቅ የሌሎችን ፍላጎትና ጥቅም ግምት ውስጥ ያስገባ አካሄድ  በመከተል ካለንበት ድህነት ለመላቀቅ እንደሚቻል ተናግረዋል ። ይህም የተጀመሩ የልማት ሰራዎች እንዲፋጠኑ ህዝብ በየተሰማራበት የስራ ዘርፍ ተረጋግቶ ውጤት እንዲያስመዘግብ  በማድረግ ረገድ ስምምነቱ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል ። በሰላም ወጥቶ መግባት የሚቻለው ሁሉም ለጋራ ጥቅምና ፍላጎት ሲስማሙ መሆኑንም ተናግረዋል ። የዞኑ ወጣቶች ማህበር ተወካይ ወጣት ኤጀታ ወርቁ የውህደት ስምምነቱ ዜጎች እርስ በእርሳቸው እንዲወያዩ፣ እንዲግባቡንና እንዲቻቻሉ በር የሚከፍት ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚረዳ ተግባር ነው ብሏል ። ስምምነቱ በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተጀመረው የዴሞክራሲ ግንባታን በማጠናከር ልማትን ለማስፈን እንደሚረዳም ተናግሯል ። አንዳንድ ሃይሎች ከግለኝነትና  ከስሜታዊነት ተላቀው የአገርን ሰላም ለማስጠበቅና የህብረተሰቡን አንገብጋቢ የኑሮ ችግር ለማስወገድ እንዲረባረቡ ሰምምነቱ የሚረዳ መሆኑንም ተናግራል ። በሌላ በኩል ደግሞ የፓርቲዎች ዉህደት ዜጎችን የአገራቸው ባለቤት ያደረገ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልፀዋል ፡፡ የፓርቲዎችን ዉህደት ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸዉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ደረጀ ማሞ እንዳሉት ስምምነቱ ህዝቦች በአገራቸው ጉዳይ የጋራ መግባባት እንድኖራቸዉ የሚያግዝ ነዉ፡፡ በአገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረዉ ፈዴራላዊ ስርዓት አጋር ድርጅቶችን አግላይ የነበረ በመሆኑ በፖለቲካዉ፣ በኢኮኖሚዉና በማህበራዊ ጉዳዮች የሚገባቸዉን ሚና መጫወት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ ''ህብረት ለሁለንተናዊ ለውጥ ምሶሶ በመሆኑ የፓርቲዎች ውህደት የ27 ዓመታት የፈዴራሊዝም ጉዞ ክፍተቶችን ከመሙላቱም በላይ ዜጎችን በአገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ነዉ'' ብለዋል፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ጥናት መምህር ካሡ ጡሚሶ በበኩላቸዉ በአገሪቱ የሚተላለፉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዉሳኔዎች በ4ቱ የኢህአደግ እህት ድርጅቶች ብቻ መከናወኑ ስህተት እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ''አሁን የተደረገዉ የፓርቲዎች ዉህደት ወቅቱ የሚፈልገዉ አሠራር በመሆኑ የህዝቦችን መብትና ጥቅም የሚያረጋግጥና ህዝቦችን የሚያቀራርብ በመሆኑ አገራዊ አንድነታችን እንዲጠናከር ያግዘዋል'' ብለዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ለአጋር ድርጅቶች ተሳትፎ መደላድል የፈጠረ በመሆኑ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ''የፓርቲዎች ውህደት ወደ ዕድገት ጎዳና የሚያመራ ካርታ ነዉ'' ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዉ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርት አምሳሌ ተክሌ ናቸዉ፡፡ ህብረት ለሁለንተናዊ ዕድገት ምሶሶ በመሆኑ ፓርቲዎች መዋሃዳቸው ለአገራችን ብልጽግና ተጨማሪ አቅም መሆኑን ገልፀዋል፡፡   አጋር ድርጅቶች በአገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ድምፅ አልባ ሆነዉ መቆየታቸዉ በገዛ አገራቸዉ ባይተዋር ከማድረጉም በላይ በአገራችን እንድነትና መቻቻል አሉታዊ ጫና ሲፈጥር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡   ዉህደቱ ለአገራችን ሰላምና የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንድፈጠር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል በማለትም ገልጸዋል፡፡    
   
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም