የትግራይ ክልል ከቤት ኪራይና ሽያጭ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አጥቷል

76
ኢዜአ ህዳር 26/ 2012  በትግራይ ክልል ከቤት ኪራይና ሽያጭ ጋር የተያያዘ መንግስት ማግኘት የሚገባውን ግብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የትግራይ ክልል ገቢዎች ልማት ባለስልጣን ገለፀ ። ቤት አከራዮችና ገዢዎች ራሳቸው ባመኑበት ዋጋ መሰረት ግብር እንዲክፈሉ የክልሉ መንግስት ቢያመቻችም መስመሩን ስቶ  ለሸፍጥና ማጭበርበር ከፍተኛ በር መክፈቱን ተገልፇል። በትግራይ ክልል ገቢዎች ልማት ባለስልጣን የግብር አወሳሰን ኦዲት ኬዝ ቲም አስተባበሪ አቶ ግደይ ናይዝጊ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከ52 ሺህ በላይ የቤት አከራዮች አሉ ። በየቀኑም የቤት ሽያጭ ስምምነቶች እንደሚፈፀሙም አስተባባሪው ገልፀዋል ። በሩብ ዓመቱ ከቤት ኪራይና ሽያጭ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም ክንውኑ ግን 67 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል ። ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ405 ሚሊዮን ብር በላይ ዝቅ ያለ ነው ብለዋል ። የችግሩ ምክንያት ደግሞ የቤት ኪራይና አከራይ ፣የቤት ሽያጭና ገዢዎች ራሳቸው ባመኑበት ዋጋ ተንተርሰው ግብር እንዲክፍሉ የክልሉ መንግስት መፍቀዱን ተከትሎ ለሸፍጥና ማጭበርበር በር በመክፈቱ መሆኑን ተናግረዋል። ግብር ሰብሳቢው አካል በቤት ኪራይና ሽያጭ የወቅቱ ገበያ መሰረት ያደረገ የራሱ ግምት በማስቀመጥ ግብር እያስከፈለ ቢቆይም ከአንድ አመት ወዲህ ግን በግብር ከፋዮች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በመደረጉ ገቢው እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል ። ከጥቂት ሰዎች በቀር አብዛኛው አከራይ ፣ ሻጭና ገዢ የተከራየው ወይም የተሸጠው ቤት ዋጋና በውልና ማስረጃ ቀርበው የሚያደርጉት ስምምነት የማይገናኝ ነው ብለዋል። ችግሩን ለማስተካከል ከአዲስ አበባና ሌሎች የተሻለ ልምድ ያላቸው ከተሞች ተሞክሮ እየወሰዱ እንደሆነ ገልጸዋል። በመቀለ ከተማ በ10 ሺህ ብር አከራይቶው በ2ሺህ ብር፣ በ5ሚልዮን ብር ሽጠው በ500ሺህ ብር እንደተሸጠ አስመስለው በመቅረብ በውልና ማስረጃ ስምምነት የፈፀሙ ግለሰቦች ይዘናል ብለዋል። በቤት አከራይና ገዢ  ከጥቂት ሰዎች በቀር አብዛኛው ትክክለኛ ዋጋ የሚናገር የለም ያሉት ደግሞ የመቀሌ ነዋሪ ወይዘሮ ታደሉ ተስፋይ ናቸው። ቤት  ተከራዮችም ትክክለኛ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳይናገሩ የኪራይ ዋጋ ይጨመርብናል በሚል ስጋት መብታቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ ብለዋል። በመቐለ ከተማ  በኪራይ ቤት የሚኖሩ ሲስተር አብረሀት ሃይሉ በበኩላቸው አከራዮች ህግና ስርዓት እንዲከተሉ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር አናሳ መሆኑን ተናግረዋል ። ችግሩን ለመፍታት ህዝብ ያሳተፈ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር መዘርጋት እንዳለበትም ሲስተር አብረሀት ጠቁመዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም