የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ የጀርመን-አፍሪካ ፋውንዴሽን ትብብር ተጠባባቂ ዋና ፀሃፊ ጋር ተወያዩ

156

ኢዜአ ህዳር 25/2012 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ መቀመጫውን ኬንያ ያደረገውን የጀርመን-አፍሪካ ፋውንዴሽን ትብብር ተጠባባቂ ዋና ፀሃፊ ሳቢኔ ኦዲሂአምቦን ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እየተጫወተች ያለውን ሚና ለዋና ፀሃፊዋ አብራርተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናን በመንገድ፣ በባቡርና አየር ትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ የበኩሏን እየተወጣች መሆኗን መግለፃቸውንም የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች በሀገሪቱ ህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትና ብሩህ ተስፋ መፈንጠቃቸውንም ሚኒስተርድ ዲኤታው አንስተዋል።

ኢኮኖሚው በሽግግር ላይ ያለ በመሆኑ ውስንነቶች ቢኖሩም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአስር አመት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ እየተካሄደ ባለው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ደስተኛ በመሆኑ የልማት ትብብርና ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ ጀርመን በቅርቡ ለኢትዮጵያ ያደረገቸው ድጋፍም የዚሁ አካል መሆኑን ዶ/ር ማርቆስ ገልጸዋል።

የጀርመን- አፍሪካ ፋውንዴሽን ትብብር ተጠባባቂ ዋና ፀሃፊ ሳቢኔ ኦዲሂአምቦ በበኩላቸው በድርጅቱና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ መሆናቸውን በመግለፅ፣ ጉብኝቱ ይበልጥ ኢትዮጵያን እንድናወቅ እድል ፈጥሮልናል ብለዋል።

የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ድርጅታቸው እንደሚያበረታታም ሳቢኔኦድሂአምቦገ ልጸዋል።