በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን የፋይናንስ ተደራሽነት አገልግሎት ማሳደግ አላማ ያደረገው መርሃ ግብር ሶስተኛ ምዕራፍ ትግበራ ሊጀመር ነው

69
ኢዜአ ህዳር 25/2012 በገጠር የሚኖሩ ዜጎች የፋይናንስ ተደራሽነት አገልግሎት ማሳደግ አላማ ያደረገው መርሃ ግብር ሶስተኛ ምዕራፍ ትግበራ እ.አ.አ በ2020 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል። የቆላ አካባቢዎችን የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ዛሬ የተጀመረ ሲሆን ኢዜአ የፋይናንስ ተደራሽነት መርሃ ግብሩን አስመልክቶ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሯል። በገጠር የሚኖሩ ዜጎች የፋይናንስ ተደራሽነት አገልግሎት ማሳደግ አላማ ያደረገው "ሩራል ፋይናንሺያል ኢንተርሚዲዬሽን ፕሮግራም" ወይም በምህፃሩ 'ሩፊፕ' ምዕራፍ ሶስት ለሰባት ዓመት የሚቆይ ነው። መርሃ ግብሩ ከድሬዳዋና አዲስ አበባ መስተዳድሮች እንዲሁም ከሐረሪ ክልል በስተቀር በቀሪዎቹ ስምንት ክልሎች በሚገኙ 300 ወረዳዎች የሚተገበር ነው። የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት ተወካይ ሀን ኡላክ ዴሚራግ እንዳሉት የኢፋድ የዳይሬክተሮች ቦርድ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ለሶስተኛው ምእራፍ የመርሃ ግብሩ ማስፈፀሚያ 40 ሚሊዮን ዶላር አፅድቋል። ከዚህም መካከል 35 ሚሊዮን ዶላሩ በድጋፍ መልክ የሚሰጥ ሲሆን የተቀረው በረጅም ጊዜ ብድር የሚከፈል መሆኑን ተናግረዋል። አጠቃላይ ለሶስተኛ መርሃ ግብር ትግበራ የሚያስፈልገው በጀት ግን 305 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የጠቀሱት ሚስ ሀን ቀሪው ገንዘብ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች የሚሰበሰብ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ በኩል ዋናው የመርሃ ግብሩ አስፈጻሚ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሲሆን ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የመርሃ ግብሩ ተባባሪ አስፈጻሚ እንደሆኑም ተናግረዋል። ሶስተኛ ምዕራፍ መርሃ ግብሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከእ.አ.አ 2020 የመጀመሪያ ሶስት ወራት ውስጥ መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። እስካሁን በተተገበሩት መርሃ ግብሮች ታቅፈው የነበሩት 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ናቸው፤ በሶስተኛው ምዕራፍ ትግበራ ግን 5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል። የዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) በኢትዮጵያ በመስኖ ልማት፣ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቃም የአርብቶ አደር ዜጎችን ኑሮ ማሻሻል አላማ ያደረጉ የፋይናንስ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አክለዋል። የ"ሩራል ፋይናንሺያል ኢንተርሚዲዬሽን ፕሮግራም" አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ዱፌራ የመርሃ ግብሩ አላማ በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ነው ብለዋል። መርሃ ግብሩ በዋንኛነት በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የገንዘብ ቁጠባ ብድር ህብረት ስራ ማህበራትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ድጋፍ የሚደረግላቸው የፋይናንስ ተቋማት የገጠሩን ክፍል የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር በመቅረፍ አኳያ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል። የፋይናንስ ተቋማት በሚደረግላቸው የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለህብረተሰቡ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነትን እንዲያስተምሩና ፋይናንስ ላይ ያላቸው ግንዛቤ እንዲሻሻል ያደርጋሉ ብለዋል። ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የገንዘብ ቁጠባ ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አቅማቸው እንዲገነባ የተለያየ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ነው አቶ ብርሃኑ ያስረዱት። የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የገንዘብ ቁጠባ ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ያላቸው የገንዘብ አቅም እንዲጠናከር በተመጣጣኝ ወለድ ሰርተው የሚመልሱት ብድር እንደሚሰጣቸውም አስረድተዋል። የፋይናንስ ተቋማቱ ለግለሰቦች በማባደር ግለሰቦቹ ገንዘብ የሚያገኙበትና ኑሯቸው እንዲሻሻል የማድረግ ተግባር እንደሚከናወንም አመልክተዋል። አዲስ ለሚቋቋሙ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የገንዘብ ቁጠባ ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አስፈላጊው የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ ይደረግላቸዋልም ብለዋል። እያንዳንዳቸው ለሰባት ዓመታት በቆዩት የቀደሙት ሁለት መርሃ ግብሮች የገጠሩ ህብረተሰብ ገንዘብ የመቆጠብ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ ማገዛቸውን ጠቅሰዋል። ተበድሮ በመስራት ኑሮን መለወጥ እንደሚቻል እንደዚሁም የተበደሩትን የመመለስ ባህልም እያደገ መምጣቱን አንስተዋል። በዚህ ረገድ የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ጠቅሰዋል። በሶስተኛ የመርሃ ግብሩ ትግበራ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና የገንዘብ ቁጠባ ብድር ህብረት ስራ ማህበራትን በገንዘብ ቁጠባ በኩል የማጠናከር ስራ በዋነኛነት ይሰራል ብለዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም