የፓርቲዎች ውህደት ለፌዴራሊዝም ስርዓት ስጋት የማይፈጥር መሆኑን ፖለቲከኞች ገለፁ

79
ኢዜአ ህዳር 25 /2012 ዓ.ም የፓርቲዎች ውህደት ለፌዴራሊዝም ስርዓት ስጋት የማይፈጥር መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ፖለቲከኞች ገለፁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) በ1980ዎቹ መጀመሪያ በአራት እህትማማች ድርጅቶች ጥምረት የተመሰረተ ግንባር ነው፡፡ ግንባሩ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢዮጵያን እያስተዳደረ ሲሆን ከአባል ድርጅቶች እና አጋር ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር 'ብልጽግና ፓርቲ' በሚል ስያሜ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት ከጫፍ መድረሱ ይታወቃል። በመሆኑም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ወደ ውህድ ፓርቲው ለመግባት የውሳኔ ሃሳብ ያሳለፉ ስምንት ድርጅቶች ሊቃነ መናብርቶች የስምምነት ፊርማ አከናውነዋል። ይህን ተከትሎ ኢዜአ 'የፓርቲው ውህደት ለፌዴራሊዝም ተስፋ ወይስ ስጋት' የሚሉ ጉዳዮችን አንስቶ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል። ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አቶ አዲስ ሀረገወይን፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አባልና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ግርማ ሰይፉ ውህደቱ ለፌደራል ስርዓት ስጋት እንደማይሆን ገልጸዋል። አቶ አዲስ ሀረገወይን የፓርቲ ውህደት ከመንግስት ሥርዓትና መዋቅር ጋር ፍጹም የተለያየ መሆኑን ገልጸዋል። የፌዴራሊዝምን ስርዓት በሚከተሉ አገሮች ላይ ያሉ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ሆነው አገር የሚያስተዳድሩ ፓቲዎች እንዳሉ በመግለጽ የፓርቲዎች ውህደት ለፌዴራል ስርዓቱ ስጋት የማይፈጥር መሆኑን አጽኖኦት ሰጥተውታል። ''ከፌዴራሊዝም ውጪ ሌላ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ስርዓት የለም ያሉት'' አቶ አዲስ፤ ነገር ግን ቋንቋ ላይ ብቻ ያተኮረው የፌዴራሊዝም ስርዓት አሁን አገሪቱ ለገባችበት ውጥንቅጥ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። ፌዴራሊዝም ቋንቋን ብቻ መሰረት ያደረገ ሳይሆን ሌሎች መለኪያዎችን ያካተተ ለአስተዳደር አመቺነትን የህዝብን ስነ ልቦና እና ታሪክን መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢዜማ አባል እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ "የኔ የሚባል ነገር ካለ ያንተ ያልሆነ ነገር አለ ማለት ነው። ከዚህ እሳቤ ወጥቶ በኢትዮጵያዊ አስተሳሰበ መደራጀት የሚያስችል ፓርቲ ማቋቋማቸው የተሻለ ነው" ብለዋል። ውህድ ፓርቲው ላይ ከወዲሁ "አሀዳዊ ነው፤ ጨፍላቂ ነው" ተብሎ የሚሰጡ ግምቶች ትክክል እንዳልሆኑ ተናግረዋል። የፓርቲውን እንቅስቃሴ ወደፊት በተግባር የሚለካ መሆኑን ያስረዱት አቶ ግርማ፤ በአዲሱ ውህድ ፓርቲ የየትኛውም ብሄር ተወላጅ ባለበት አካባቢ ፓርቲውን መቀላቀል የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አብራርተዋል። ይህ ደግሞ ዜጎች በብሄር መደራጀት ሳያስፈልጋቸው ለአገራቸው አስተዋጽኦ ማበርከት የሚፈልጉ ማንኛውም ግለሰቦች ባሉበት አካባቢ ይሄን አንድ የሆነ ፓርቲ በመቀላቀል ማገልገል የሚያስችል መሆኑ ጥሩ እድል መሆኑን ገልፀዋል። የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ የፓርቲዎች ውህደት ለፌዴራሊዝም ሥርዓት ስጋት ይፈጥራል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ነገር ግን አዲሱ ውህድ ፓርቲ  መነሻው አሁን ያለው ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አወቃቀር ለችግሮች መንስኤ ነው ብሎ መሆኑና የወደፊት አቅጣጫውስ በምን መልኩ ይጓዛል የሚለው ስጋት እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም። ቋንቋን፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና ሌሎች የመሳሰሉ መርሆችን ጨምሮ ከቡድን መብት ይልቅ የግለሰብ መብትን ማስቀደሙ፤ በማንነታቸው ምክንያት በደል ደርሶብናል ለሚሉ አካላት፤ በቂ የሆነ መልስ ሊሰጥ በሚችልበት መልኩ ይንቀሳቀሳል ብለው እንደማያምኑ እና ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል። የራስን ቋንቋና ባህል የማዳበር ሁኔታዎች በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አወቃቀር የተሻለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ በቀለ አሁን ላይ በአገሪቱ ለሚታዩ ውጥንቅጦችና ውዝግቦች መነሻቸው ከዚህ ከህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙ ጋር የተያያዙ አይደሉም ብለዋል። ይልቁንስ አገሪቱ አሁን ላለችበት ውጥንቅጥ መንግስትን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን ለዚህም ጠንካራ መንግስት ያለመኖር፣ ስነ ስርዓትን እና ህግን ማስከበር ያለ መቻል እና ህገ መንግስቱን ስራ ላይ ማዋል እና መተርጎም ላይ ክፍተት በመኖሩ ነው ብለዋል።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም