ውህደቱ ጨፍላቂ ሳይሆን በሃገራዊ ጉዳዮች የሚያሳትፍ ነው፡- የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብልፅግና ፓርቲ አባላት

57
ኢዜአ ሕዳር  25 /2012  ውህደቱ ጨፍላቂ ሳይሆን በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያሳትፍ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን ፈፅመነዋል ሲሉ የቤኒንሻጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ አባላት ተናገሩ፡፡ በፓርቲው አጠቃላይ ፕሮግራሞች ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ተከሔዷል፡፡ በመድረኩ ከተሳተፉት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አቶ ሃሰበላ አዜን እንደገለፁት “ውህደቱ ለዘመናት ስናስበው የነበረውና ጠቀሜታው ተገንዝበን የፈጸምነው በመሆኑ ምንም ብዥታ አልፈጠረብንም” ብለዋል፡፡ በአንድ ሃገር የተለያየ የመንግስት አደረጃት እንጂ ሃገር የሚመራ ፓርቲ የተለያየ ቅርጽ እንደሌለው የተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ ያሳያል ያሉት አስተያየት ሰጪው ግንባሩ ሲከተለው የኖረውን አካሔድ “ፍጽም አግላይ ነበር ” ሲሉ ኮንነነዋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ አግላይ አካሄድ አይከተልም ያሉት አቶ ሃሰበላ ውህደቱን ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ “አዲሱ የፓርቲው ቅርጽ ጨፍላቂ ነው” በሚል በጥቂት ግለሰቦች የሚነዛው ወሬ መሠረት የሌለው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አሁን ብዥታ ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ከዚህ ቀደም የግል ጥቅማቸው በማስቀደም ህዝቡን ሲያደናግሩ የቆዩ እንደሆኑም አብራተዋል፡፡ በቀጣይ በየትኛውም የክልሉ ነዋሪ ላይ የሚፈጸም በደል ቢኖር እንኳን ለችግሩን ቀዳሚ ሃላፊነት ወስደን መፍታት ያለብን እኛ ነን ሲሉ አቶ ሃሰባላ ተናግረዋል ፡፡ ጠንካራ ሃገረ መንግስት እንደምንሆን አልጠራጠርም ያሉት ደግሞ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ ሲሆኑ ህብረተሰቡን በውህደቱ ላይ የጠለቀ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ቀሪ የቤት ስራ ይሆናል ብለዋል፡፡ “በመደመር 20 ዓመት የከረመ የህዝባችን ጥያቄ ተመልሷል” ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙስጣፋ መሃመድ ናቸው፡፡ የፌደራሊዝምን ስርዓት በሚቃረን መልኩ “መተከል የእኛ ነው” በሚል የሚቀሰቅሱ ጽንፈኞችን ስርዓት ማስያዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገለታ ሃይሉ በበኩላቸው የብልጽግና ፓርቲ አካታችነትን በተግባር እንዳሳየ ጠቅሰው የውህደቱ ዋነኛ አስፈላጊነትም ይኸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ “ውህደቱ እጅግ ቢዘገይ እንጂ አልፈጠነም” በሚል ሃሳባቸውን የሚያስቀምጡት ደግሞ አቶ ዚያድ አብዱላሂ የተባሉ ተሳታፊ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ውህደቱ የክልሉ አመራሮችም ሆኑ ህብረተሰቡ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲታዩ የነበረውን አግላይ አካሄድ በማስቀረት እኩልነትን ያረጋግጣል፡፡ ህገ-መንግስቱ ሁሉንም ዜጎች እኩል እንደሆኑ በግልጽ ቢያስቀምጥም የቀድሞው ኢህአዴግ ግን በዚሁ መንገድ ሲያገለግል እንዳልነበረ ጠቅሰዋል፡፡ በውህዱ ፓርቲ አካሄድ በድርጅት እና በመንግስት መካከል ያለውን መደበላለቅ በግልጽ ማስቀረት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡ ክልሎች በተለያየ የእድገት ደረጃ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ዚያድ ይህን የኢኮኖሚና ሌሎችንም ልዩነቶች በማቀራረብ አካታችነትና ፍትሃዊነትን በተግባር ማረጋገጥ ግድ ይለናል ብለዋል፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደገለፁት በየትኛውም ዓለም ተሞክሮ የፖለቲካ ድርጅት የዚህን ዓመት ያህል ግንባር ሆኖ ቆይቶ አያውቅም ብለዋል ። ውህደቱን ስንጠይቅ የኖርነው ፓርቲው አቃፊ እንዲሆን ለማድረግ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በአገር መሪነት መምረጥና መመረጥን ጨምሮ ሳንሳተፍ የቆየንበት አግላይ ምዕራፍ በውህደቱ ተዘግቷል በማለት አብራርተዋል ። አክለውም ከለውጡ በፊት የተመረጡ የግንባሩ መሪዎች በምርጫው ሂደት ስላልተሳተፍን እምነት አልነበረንም ሲሉ ተናግረዋል ። “ከዚህ ቀደም ግንባሩ ጉባኤ ሲያካሔድ የክልሉን ህዘብ ወክዬ ብገኝም ጡረታ ከወጡ አባላት ጋር በአንድ ጎን ተቀምጬ የአመራር ምርጫ ሲካድ እንደታዛቢ እከታተል ነበር” በማለት ያስታውሳሉ ። ውህደቱ ባይፈጸም አጋር ድርጅቶች በነበረው አካሄድ መቀጠል አይችሉም ነበር ያሉት አቶ አሻድሊ በድርጅቶቹ መካከል የተፈጠረውና እየሠፋ ሄዶ ለሃገር ስጋት የሆነውን ጫፍ የረገጠ አካሄድ እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡ “አንዳንድ የግንባር ድርጅቶች የራሳቸውን ብሔር ብቻ ተጠቃሚነት በማጉላት ሌላውን የረሱ ነበር” ያሉት አቶ አሻድሊ ውህደቱ የብሔር ማንነትንና ሃገራዊ አንድነትን ያጣጣመ ነው ” ሲሉ አውስተዋል፡፡ አገር ሊበትን የሚችል በብሔር ድርጅቶች መካከል ያለውን ጫፍ የረገጠ የእርስ በርስ መጠራጠር እንዲቆም መደረጉንም አስረድተዋል ። “በክልሉ የፌደራሊዝምን ስርዓት ለማፍረስ የሚመጣን አካል የሚቀበል መንግስትም ሆነ ህዝብ የለም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ በፓርቲና በግለሰብ ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን በጠንካራ ዴሞክራሲ አንድነት የተገነባች ሃገር መገንባት የፓርቲው ዋነኛ የቤት ሥራ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ የንቅናቄ መድረኩ በክልሉ እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ የሚዘልቅ ነው ተብሏል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም