የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ባሕሪ እየጎለበተ የመጣ ቢሆንም አሁንም ብዙ መሻሻሎች ይቀሩታል - ፖለቲከኞች

76
ኢዜአ ህዳር 25 / 2012 ዓም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ባሕሪ እየጎለበተ የመጣ ቢሆንም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን ጨምሮ የተለያዩ እንቅፋቶች እየገጠሙት እንደሆነ ኢዜአ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገለፁ። አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከተጀመረበት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መስተጋብር የመሰልጠን ባሕሪ እያሳየ ነው። ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመደራጀት መብቶች ከዴሞክራሲ መገለጫዎች መካከል ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን የሚናገሩት ፖለቲከኞቹ በዚህ ረገድ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በአገሪቱ የተወሰዱት እርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው ይላሉ። በአገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ መጫወቻው መድረክ ነፃና ሰፊ ይሆን ዘንድ የተወሰደውን እርምጃም ያደንቃሉ። የትግራይ ዴሞክራሲዊ ትብብር (ትዴት) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግዴይ ዘርዓጺዮን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እየታዘቡ መሆኑን ገልፀዋል። እንደእርሳቸው ገለጻ ለውጡ በተጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታታቸው ጥሩ እርምጃ ነው። ከዚህም በላይ የመገናኛ ብዙሃን በአንጻራዊነት ነጻ ሆነው መስራት ጀምረዋል፣ በስደት በውጭ አገራት ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል። "ከሁሉም በላይ ግን  በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሻሻለ የመጣውን የፖለቲካ ሁኔታ ተጠቅመው ወደ አንድነት መምጣታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው"  ሲሉም የትዴት ምክትል ሊቀመንበር ገልፀዋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው በአገሪቱ የፖለቲካ ማህበራትና ቡድኖች ዘንድ የተንሰራፋው አለመደማመጥ ችግር አሁንም አልተፈታም። ይህም የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን ከማበላሸት አልፎ ሕዝቦች መካከል ጥላቻ ላይ ያነገበ ልዩነት እንዲመጣ እያደረገ ነው ብለዋል። በቅርቡ እየተለወጠ በመጣው አጠቃላይ የአገሪቷ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ግን በተለያየ ጽንፍ ላይ የቆሙ የፖለቲካ ድርጅቶች መቀራረብና መወያየት ጀምረዋል ሲሉም አመልክተዋል። እነዚህ የአገሪቱን ዴሞክራሲ ለማጠናከር የሚያግዙ መልካም ክስተቶች ቢሆንም ፖለቲካው አሁንም ስጋቶች የተገረጡበት መሆኑን የትዴት ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ግዴይ ያብራራሉ። የተጀመረውን መልካም ጉዞ ወደ ኃላ የሚጎትቱ ክስተቶች በተለያየ መልኩ እየታዩ በመሆኑ ትኩረት እንደሚያሻ ገልጸዋል። በቅርቡ ከፀደቀው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ አዋጅ ጋር በተያያዘ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ የሚስተዋለው አለመግባባት ቀላል ግምት ሊሰጠው አይገባም ሲሉም አሳስበዋል። ምክንያቱም ይህ ውዝግብ በተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊኖረው እንደሚችል ነው አቶ ግደይ የሚናገሩት። የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ በበኩላቸው ፖለቲካ በየትኛውም ሁኔታ በለውጥ ላይ ከሆነ የተለያዩ ውስብስብ ችግሮች እንደሚያጋጥሙት ይጠበቃል ሲሉ ያስረዳሉ። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው በተለያየ ጎራ የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች ተሰባስበው ሂደቱ ወደየት እንደሚያደርስ ገምግመው አቅጣጫ ማስቀመጥን ይጠይቃል ብለዋል። ይህ ካልሆነ ተስፋ የተጣለበትን የአገሪቱ የፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ማጨለምና ወደኋላ መመለስ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩት የፖለቲካ ችግሮች ወዳልተፈለገ የጥፋት አቅጣጫ እንዳይሄዱ በአግባቡ ይፈቱ ዘንድ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ኢዜአ ያነጋገራቸው እነዚህ ፖለቲከኞች አክለውም አሳስበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም