የኢትዮ-ኤርትራ አዲስ አጋርነት ቀጠናዊ ስትራቴጂክ ጥቅም ይሰጣል-ምሁራን

66
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ አጋርነት በቀይ ባህርና አፍሪካ ቀንድ ህዝቦች እስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማረጋገጥ አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ገለጹ። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ላለፉት 20 ዓመታት የነበራቸውን 'ሞት አልባ ጦርነት ' ለመቋጨት የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ፓኬጁን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ የልዑካን ቡድን እንደሚልኩ በኤርትራ  የሰማዕታት በዓል ላይ ባስተላለፉት መልእክት ይፋ አድርገዋል። ያም ብቻ ሳይሆን የኤርትራ ቀጣይ እጣ ፈንታም ኤርትራ ከጎረቤት አገሮች በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው ግንኙነት ላይ የተወሰነ መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያረጋገጡት። ኢዜአ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የፖለቲካ ተንታኞችን አስተያየት ሰብስቧል። በመካከለኛው ምስራቅ ጂኦ-ፖለቲክስና የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዳዲ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለሁለቱም አገሮች ዘላቂ ሰላምና ጥቅም መረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን አሳይታለች። እንዲያውም ለሠላም ድርድሩ ሲባል መቅረብ ከሚገባት ከግማሽ መንገድ በላይ በመቅረብ እርቅ ማውረድ እንደምትፈልግ በተግባር አረጋግጣለች ነው ያሉት። ኤርትራ በቀይ ባህር ዋነኛ ተዋናይ መሆኗ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗ አገራቱ በቀጠናው ያላቸውን ከፍተኛ ድርሻ ያመላክታልም ብለዋል አቶ ዳዲ። ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የግዙፍ ምጣኔ ኃብትና ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የያዘች መሆኗም ሌላው ሁለቱን አገራት እስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመመስረት የሚያስችል ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል። የአገራቱ አጋርነት በአሁኑ ወቅት በቀይ ባህር አከባቢ እየታየ ያለውን የተለያዩ አገሮች ወታደራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ውድድር እንዲሁም የሰላም ስጋት ከማስቀረት አኳያም ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። የጋራ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ከማረጋገጥ ባለፈም የጋራ ደህንነት ዋስትና በመስጠትም ጭምር ስምምነታቸው አዎንታዊ ተጽዕኖም ይኖረዋል ነው ያሉት። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ዘላቂ ሰላም ማስፈን በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰላምና መረጋጋት በማስፈንና ግጭት በመፍታት በኩልም ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አበበ አይነቴ ናቸው። በመሆኑም የኢትየጵያ ፖሊሲና እስትራቴጂ ከኤርትራ በምታደርገው ዘላቂ ሰላም ድርድር ጋር የተቃኘ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ። በምስራቅ አፍሪካ በመሰረተ ልማትና ኃይል የማስተሳሰር ሥራን በማቀላጠፍ በቀጠናው ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመገንባት የተጀመረው እንቅስቃሴም ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል። የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ለሰላም ጥሪው ለሰጡት መልካም ምላሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። "አገሪቷ የሰማዕታት ቀን በምታከብርበት ዕለት ያሳዩት በጎ ምላሽም ለሁለቱ አገራት የሚጠቅምና የሚደነቅ ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሞካሽተዋቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም