ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድን በተመለከተ ስልጣን ባይሰጠንም አብረን እንሰራለን - አቶ ዘነበ

151

ኢዜአ ህዳር 24/2012 ''10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድን በተመለከተ በአዋጅ ስልጣን ባይሰጠንም አብረን እንሰራለን'' ሲሉ የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ ለስራ ዕድል ፈጠራ መልካም አጋጣሚ ነው።

የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱን በተመለከተ በአዋጅ ስልጣን የተሰጠው በአደረጃጀት እንዲፈርስ የተደረገው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ለህጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ሚኒስቴር መሰጠቱን ገልዋል።

ይህም ሆኖ ለኤጀንሲው በአዋጅ የተሰጠው ሃላፊነት ባይኖርም ብድር ከሚሰጡ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱን በተመለከተ ያለው አሰራር ላይ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት ለሚመለከተው አካል እንደቀረበ የገለጹት አቶ ዘነበ፤ ተደራጅተው ብድር የሚሰጣቸው ወጣቶች ቁጥር በአምስት ብቻ ከሚገደብ እስከ ሶስት ድረስ ቢፈቀድ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ አማራጭ መቅረቡን ጠቁመዋል።

በኤጀንሲው የቀረበው የማሻሻያ ሃሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል የሚል እምነት ያላቸው ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኤጀንሲው ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያገኝበት ስርዓት ቢፈጠር የስራ ዕድል ፈጠራውን እንደሚያቀላጥፈው ተናግረዋል

የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ላይ የሚታዩ ችግሮችን መገምገም አስፈላጊ እንደሆነ አመልክተው፤ ወጣቱን ገንዘቡን ወስዶ ህይወቱን የሚቀይርበት መሆን እንዲችል ክትትል መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ብድሩ በነጻ የሚሰጥና የማይመለስ እንዳልሆነ አድርጎ መገንዘብ የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነም አቶ ዘነበ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም