''ፕሮ ሆልስቲክ አፍሪካ '' የትግራይ ብስክሌት ስፖርት ለማጠናከር እንደሚሰራ ገለፀ

84
ኢዜአ ህዳር 24/12 ዓ/ም--''ፕሮ ሆልስትክ አፍሪካ'' የተባለ የስፔን መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ተቋም ከትግራይ ክልል ብስክሌት ፌዴሬሽን ጋር ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ። ''የስፔን ሆልስቲክ አፍሪካ ተቋም'' አስተባባሪ ሚስተር ፓውሎ መሬስ ዛሬ በዓዲግራት ከተማ ተገኝተው እንደተናገሩት የትግራይ ብስክሌት ስፖርትን ለማጠናከር ከፌደርሽኑ ጋር ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት አለው ። የትግራይ የመሬት አቀማመጥ ለብስክሌት ስፖርት  አመቺ ነው ያሉት አስተባባሪው በኮርስና በማውንቴን ብስክሌት ውድድር የሚሳተፉ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተቋማቸው የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ተዘጋጅቷል ። በስፔን በብስክሌት ስፖርት የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን ለትግራይ ብስክሌተኞች ለማካፈል እንደሚሰራም አስተባባሪው ተናግረዋል ። ስፖርቱን ለማሳደግ የሚረዱ የብስክሌት መለዋወጫ ሄልሜት፣ የውድድር ሽራብ፣ የቴክኒክ አቅምና የስነልቦና ትምህርቶች በመስጠት ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል ። የትግራይ ክልል ብስክሌት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ታደሰ ነገሽ በበኩላቸው ድጋፉ የክልሉ የብስክሌት ስፖርትን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል። እንዲሁም በስፖርት ዘርፉ ክልሉንና ሃገራችንን የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት የበኩሉን እገዛ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ተቋሙን ወክለው ወደ ትግራይ ክልል ከመጡ አንጋፋ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች መካከል እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር   በ1988  የቱር ደፍራንስ አሸናፊና በቮልታ እስፓኛ በ1985 እና በ1989 አሸናፊ የሆነው እንቁ ብስክሌተኛ ፔድሮ ቤርጋዶ እና ሌሎች አንጋፋ ስፖርተኞች ይገኙበታል። የስፔን ልኡካን ቡድን በቆይታቸው ከትግራይ ብስክሌተኞች ጋር በመሆን እስከ መጪው ዓርብ ድረስ በሚካሔደውና ከመቐለ እስከ እንትጮ ከተማ ድረስ 200 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የብስክሌት ውድድር ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም