የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

83
ኢዜአ ህዳር 24/2012 አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ተጠቃሚነታቸውነ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አስታወቀ። አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አስታወቀ። አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን “የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና መሪነት በማጎልበት የ2030 የልማት አጀንዳ ውጤታማነት እንረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል ትናንት በሻሸመኔ ከተማ ተከበረ። በአለም አቀፍ ደረጃ ለ28ኛ በኢትዮጵያ ለ27ኛ ጊዜ በተከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት ነው የተከበረው። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበዓሉ ላይ እንዳሉት መንግስት አካል ጉዳተኞችን ያካተተና ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጠ ስርዓት በመዘርጋት በትኩረት እየሰራ ነው። የአካል ጉዳተኞችን መሰራታዊ ችግሮች በመለየት ከስር መሰረቱ መፍታት የሚቻለው የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑን ገልጸዋል። አካል ጉዳተኞችን በፖለቲካው መስክ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ጠንካራና ተደራሽ የሆነ አደረጃጀት ዕውቀትና ሀብት መረጃና ግብዓት ቅንጅትና ትብብር አብዘቶ ይጠይቃል ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን የመኖሪያ ቤትና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከጤና አንጻር አካል ጉዳተኝነትን መከላከል፣ የአካል ድጋፍ የማድረግና ገቢ የሌላቸውን አካል ጉዳተኞችን ነጻ የህክምና አገልግሎት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪ የተሀድሶ ማዕከላትን በማደራጀት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልፀው በትምህርቱ መስክም የአካቶና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶችን በመክፈት እየሰራ እንደሚገኝና ይህንንም ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። ከስራ ስምሪት አንጻር አካል ጉዳተኞች እንደችሎታዎቻቸውና ፍላጎታቸው በቅጥር፣ በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል። ክልሉ በነበረው ለየት ያለ አቋም የዜግነት አገልግሎት አዋጅ በማጽደቅ ድጋፍ እንደተደረገ እንደሚገኝ ገልጸል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ እንዳሉት አካል ጉዳተኞችን በማብቃትና በሁሉም መስኮች በማሳተፍ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግ ይገባል። አካል ጉዳተኞችን የለውጡ ተሳታፊም ተጠቃሚም በማድረግ አካታችና ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚደረገውን ሂደት ለማፋጠን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትጋት መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በእኩልነት የምታቅፍ የሁሉ እናት ሆና እንድናያት ለአንዳንዱ ያለገደብ ለሌላው አቅም በፈቀደ የምንደርስበትን የልማት አካሄድ ትተን ሁሉን አቀፍና ማንም ወደ ኋላ የማይቀርበትን የልማት እርምጃ ልገምር ይገባል ብለዋል። በበዓሉ ላይ ያለድጋፍ መንቀሳቀስ ለማይችሉ አካል ጉዳተኞች ዊልቸር በስጦታ የቀረበላቸው ሲሆን የሚቀጥለው አመት የሚከበረውን አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ለማክበር የአማራ ክልል ተመርጧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም