ተቋማቱ የሰላም ማዕከላት ሊሆኑ እንደሚገባ ተመለከተ

64
  ሚዛን ግንቦት 1/2010 የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግልጽ የሆነ አሰራር በመዘርጋት የሰላም ማዕከላት ሊሆኑ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰባተኛው የሰላም ፎረም በሚዛን አማን ከተማ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የክልሉ ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ አንጎ  በፎረሙ መድረክ በመገኘት "ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራውን ሰላማዊ በማደረግ የሰላም ማዕከል መሆን አለባቸው "ብለዋል፡፡ ግጭት ከመከሰቱ አስቀድሞ በመከላከልና ችግሮች ሲፈጠሩም ፈጣን መፍትሔ በመውሰድ የትምህርት ሂደቱ እንዳይስተጓጎል በማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ሰላም የሚረጋገጠው በአንድ አካል ብቻ ሣይሆን የዩኒቨርሲቲ አመራሩ ፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞችን ጨምሮ ሁሉም በያለበት የድርሻውን ሲወጣ መሆኑን አቶ አድማሱ ገልጸዋል፡፡ በፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር የሠላም እሴቶች አስተምህሮ ዳይሬክተር ጀኔራል አማካሪ አቶ ቴዎድሮስ ፍስሐ በበኩላቸው ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ የሚቻለው ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ከመሰረታቸው መፍታት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግልጽ የሆነ አሰራር መዘርጋትና መፍጠር ሌላኛው የግጭት መከላከያ ዓይነተኛ መንገድ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የቤተመጻሕፍት፣ የውሃ ፣ የምግብና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ክፍተት አብዛኛውን ጊዜ በተማሪዎች ቅሬታ የሚነሳባቸው ጉዳዮች  መሆናቸውን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ፎረሞቹ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ " ዩኒቨርሲቲዎች ተገናኝተው መምከራቸውም አንዳቸው ከሌላው ልምድና ተሞክሮ እንዲለዋወጡ ያግዛቸዋል" ብለዋል፡፡ ለሶስት ቀናት የሚቆየው የሠላም ፎረሙ በግጭት መከላከልና አስተዳደር ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በምሁራን ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ በፎረሙ በክልሉ የሚገኙ አስር የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም