የወላይታ ሶዶ ከተማ ለ20 ማህበራት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አስረከበ

139
ኢዜአ ህዳር 24/03/2012 የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከ2009 ዓም ጀምሮ ሲጠባበቁ ለነበሩ 20 ማህበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ዛሬ አስረከበ፡፡ የከተማው አስተዳደር እንደገለፀው አነስተኛ ገቢ ላላቸውን ዜጎች በተለይ ለመንግስት ሠራተኞች በሊዝ መነሻ ዋጋ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ማቅረብ ያስፈለገው እየተነሳ ያለውን ቅሬታና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ነው ። የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ምክትል ካንቲባ አቶ ያለው ጌታቸው ዛሬ መሬት የተረከቡት 20 ማህበራት መሬቱን ለመረከብ ረጅም ጊዜ እንዲጠብቁ የተደረገው ከባለቤትነት ነጻ የሆኑ መሬቶችን አቅርቦት ማነስና ፤ካሳ ከፍሎ ለማስለቀቅ የገንዘብ እጥረትና የትኩረት ማነስ በመኖሩ መሆኑን ገልፀዋል ። አሁን ላይ አስተዳደሩ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ነዋሪዎች በተለይም የመንግስት ሠራተኞችን በሊዝ መነሻ ዋጋ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ በማቅረብ ተጠቃሚ የማድረጉን ተግባር በልዩ ትኩረት እንደሚሰራና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል ። ላለፉት ሶስት ዓመታት የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው አስተዳደሩ የገባውን ቃል በአግባቡ ሳይፈጽም በመቅረቱ ለእንግልት ተዳርገዉ የነበሩ በቁጥር ከ200 በላይ የሆኑ ነዋሪዎች ከ2 ነጥብ 8 ሄክታር በላይ መሬት ከነሳይት ፕላኑ እንዲረከቡ አድርጓል ። ማህበራቱ በተለያዩ ምክንያቶች መሬቱን ሳይረከቡ መቆየታቸውን የፈጠረው እንግልት ለማካካስ በአፋጣኝ ቤታቸውን ገንብተው መኖር እንዲችሉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላትና ድጋፍና ክትትል በማድረግ ተገቢውን እገዛ እንደሚደረግላቸው የሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኬያጅ አቶ በረከት በቀለ ገልፀዋል ፡፡ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ከተሰጣቸው መካከል መምህርት ነፃነት ሰሎሞን እንደገለፁት 14 ሆነው ድል በጊዜው የሚል የመኖሪያ ቤት ማህበር በመመስረት ያቀረቡትን የቦታ ጥያቄ አሳማኝ መልስ ሳይሰጣቸው ለሶስት ዓመታት ያክል እንደተንገላቱ ተናግረዋል ። አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ ቅሬታቸውን በመፈታቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል ። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በከተማው ሲንከባለሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ቅሬታዎች ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን አሳታፊ በሆነ መልኩ እየለየ መፍትሄ ለመስጠት በአስተዳደሩ በኩል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም መምህር ነጻነት አስረድተዋል፡፡ ማህበራቱ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ቢያሟሉም በቂ ምላሽ የሚሰጥ ማጣታቸውን የሚመለከት ዘገባ ተሰርቶ እንደነበር ይታወሳል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም