አለም አቀፉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ማህበር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

75
ኢዜአ ህዳር 24/2012 13ኛው አለም አቀፍ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ማህበር ጉባኤ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ባለፈው ዓመት በእንግሊዝ ለንደን በተካሄደው 12ኛው የማህበሩ ጉባኤ ላይ ከስዊዲንና ብራዚል ጋር በእጩነት ቀርባ ነው። "ለድንበር ተሻጋሪ የህብረተሰብ ጤና ችግሮች በመረጃ የበለጸገ ዓለም አቀፍ እርምጃ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የዘንድሮ ጉባኤ የተለየዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና 150 የዓለም የሕብረተሰብ ጤና ድርጅት አባል አገሮች ተወካዮች እየተሳተፉበት ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በዚሁ ወቅት አንደገለጹት፤ ጉባኤው በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጤና ዙሪያ ባሉ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይመክራል። በተለይም በድንበር ተሻጋሪ የህብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሳይንሳዊ ምልከታና ቴክኒካዊ ሂደቶችን የሚዳስስ መሆኑንም ገልጸዋል። በአጠቃላይ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጤና ተግዳሮቶች ላይ ጉባኤው መክሮ የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚያስቀምጥም ተናግረዋል። የአለም አቀፉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አንድሬ ቫን፤ ''ጉባኤው ድንበር ተሻጋሪ የህብረተሰብ ጤና ጉዳይ በርካታ የአለም አገሮችን ያሰባሰበ ነው'' ብለዋል። ይህም አገሮች ያላቸውን ሙያዊ ልምድ እንዲለዋወጡ ይበልጥ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል። የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሁለት አስርታት ተኩል ውስጥ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል። በተለይም በህብረተሰብ ጤና መሻሻል ላይ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበች እንደሆነ ተናግረዋል። ''የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ሚኒስቴር የቴክኒክና የሳይንሳዊ ተግባራት ዋና ድጋፍ ነው'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለህብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት የላቦራቶሪ አገልግሎት በመስጠትና ምርምር በማካሄድ ጠንካራ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም የጤና ሚኒስቴር የተቋሙን አቅም ይበልጥ ለመገንባት ያልተገደበ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል። ዘንድሮ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ከደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያና ሞሮኮ ቀጥሎ በአፍሪካ ሲካሄድ አራተኛው ነው። ዓለም አቀፉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ95 አገሮች የሚገኙ 108 አባላት ያሉት ሲሆን አምስት ቢሊዮን ሕዝቦችንም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን መረጃዎች ያመላክታሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም