በጎንደር ከተማና ዙሪያው ግጭት በመፍጠር የተጠረጠሩ 156 ሰዎች ለህግ ቀረቡ

111

ኢዜአ ህዳር 24 ቀን 2012 በጎንደር ከተማና ዙሪያ የገጠር ቀበሌዎች በቅርቡ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተጠረጠሩ 156 ግለሰቦች ለህግ መቅረባቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

የከተማውን ሰላምና ደህንነት አስመልክቶ ትናንት በተካሄደ የውይይት መድረክ በቀረበ ጥናታዊ መረጃ እንደተጠቆመው በግጭቱ የ43 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በዘጠኝ ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

የከተማው አዴፓ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ ባቀረቡት የጥናት ሪፖርት እንደገለጹት ተጠርጣሪዎችን ለህግ ማቅረብ መቻሉ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው ።

ለህግ ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል የግጭቱ ጠንሳሽና ተዋናይ መሆናቸውን በማስረጃ የተረጋገጠባቸው 14 ግለሰቦች የእስር ቅጣት ተበይኖባቸው ማረሚያ ቤት መግባታቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች 27 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው ሲሆን 17 ተጠርጣሪዎች ምርመራቸው ተጣርቶ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስረድተዋል።

98 ተጠርጣሪዎች ደግሞ ተይዘው ለህግ ቢቀርቡም ተጨባጭ ማስረጃ ባለመገኘቱ በነጻ እንዲለቀቁ መደረጉን አመልክልተዋል።፡

በግጭቱ ከስምንት ሺህ በላይ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው ከዚህ ውስጥ ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደቀያቸው ተመልሰዋል።

ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በ145 ግለሰቦች ቤት ንብረትላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በአጠቃይ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን ከኃላፊው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል ።

የከተማውን የቀደመ ሰላም ወደ ነበረበት በመመለስ በኩል ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላምና ልማት ሸንጎ፣ አመራሩና የጸጥታ መዋቀሩ ግንባር ቀደም ሚና ነበራቸው ተብሏል፡፡

የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸው በከተማው ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋትና የሰላም እጦት በንግድ ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፎ አልፏል፡፡

የሰላም መደፍረሱን ተገን በማድረግ ህገ ወጥ ግለሰቦች በከተማው የግንባታና የኢንቨስትመንት መሬት ላይ ወረራ መፈጸማቸውን ጠቁመው በአጥፊዎች ላይ ጥናትን መሰረት ያደረገ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናገረዋል፡፡

የተቀዛቀዘውን የከተማውን የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማጠናከር እንዲቻልም ከስድስት ዓመት በላይ የኢንቨስትመንት ቦታ አጥረው የቆዩ 20 ባለሀብቶች የወሰዱትን ቦታ እንዲቀሙ መደረጉን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል ።

በክፍለ ከተሞችና በአገልግሎት ጽህፈት ቤት ባለጉዳይን በማጉላላትና ሙስና በመፈጸም ህዝብ እንዲማረር ያደረጉ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ከስራ እንዲታገዱ መደረጉንም ከተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

የክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት የጎንደር ከተማን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የክልሉ መንግስት አዳዲስ አመራሮችን ከመመደብ ጀምሮ የቅርብ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው ብለዋ፡፡

የከተማው ሰላም አሁን ላይ በተሻለ ደረጃ እንደሚገኝ የጠቆሙት የቢሮ ሃላፊው ህዝቡና መንግስት እጅና ጓንት በመሆን ለሰላም ግንባታው በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም