በብልጽግና የፓርቲ ውህደት አስፈላጊነትና የቀጣይ ትግል አቅጣጫ ዙሪያ ውይይት እየተካሔደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በብልጽግና የፓርቲ ውህደት አስፈላጊነትና የቀጣይ ትግል አቅጣጫ ዙሪያ ውይይት እየተካሔደ ነው
59
ሀዋሳ ህዳር 24/2012 ኢዜአ.... በብልጽግና የፓርቲ ውህደት አስፈላጊነትና የቀጣይ ትግል አቅጣጫ ዙሪያ የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ተጀመረ። በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት የፓርቲዎች ውህደት የውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲንና ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ለማጠናከር አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባትና አቅምን ለማሰባሰብ ያግዛል። ደኢህዴን 21 ብሄራዊ ድርጅቶችን በአንድ ላይ በማዋሀድ ላለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት በክልሉ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደቻለ ገልጸዋል። ደኢህዴን ለውህደቱ እንደ ትልቅ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ውህደቱ አሀዳዊ ስርዓት ያመጣል ለሚሉ ምላሽ እንደሚሆን ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ በስድስት ቡድን በመከፋፈል የፓርቲ ውህደትና የቀጣይ ትግል አቅጣጫ በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ማድረግ ጀምረዋል። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች አመራሮች ፣ ቢሮ ሀላፊዎች ፣ የዞንንና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎችና የመምሪያ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።