የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ግልጽ የሆነ የፖሊሲ አማራጭ ለህዝብ ለማቅረብ ዕድል ይፈጥራል - ፖለቲከኞች

68

ኢዜአ ህዳር 23/2012 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት መፈጸም ግልጽ የሆነ የፖሊሲ አማራጭ ለህዝብ ለማቅረብ ዕድል እንደሚፈጥር የሁለት ፖለቲካ ፓርቲ ሊቃነ መናብርት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በተለይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ህዝቡ ግራ ሳይጋባ የቀረበለትን ግልጽ የፖሊሲ አማራጭ በቀላሉ ለመምረጥ ያስችለዋል።

የፓርቲዎች ውህደት መፈጸም የተሻለ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅምን ከማጠናከር ባሻገር በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳር የተሻለ ስብስብ እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ የሺዋስ ገለጻ፤ የዳበረ የዴሞክራሲ ዕድገት ባለባቸው የአውሮጳና የእስያ አገሮች ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ከሦስት አይበልጡም።

የተለያየ ሀሳብ ያላቸውን ፓርቲዎች ወደ አንድ በማምጣት ውህደት መፈጸም ፈታኝ እንደሆነ የገለጹት አቶ

የሺዋስ ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/እና አጋር ፓርቲዎች ውህደት ሲፈጽሙ ችግር ሊገጥም እንደሚችል ይታወቅ እንደነበር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ከሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቀላሉ ውህደት መፈጸም

የቻለው ከዚህ በፊት በኀብረት፣ በአማራጭ ኃይሎች፣ በቅንጅትና በመድረክ ተሰባስቦ በጋራ የመስራት ልምድ ያካበተ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ /መድረክ/ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ የፓርቲዎች ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ መሰባሰብ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ውህደት በስምምነት እንጂ በግዳጅ ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሌለበትም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት መጠናከር የፓርቲዎች መሰባሰብ አስፈላጊ መሆኑን ፕሮፌሰር መረራ ገልጸዋል።

''በተለይ የፓርቲዎች መሰባሰብ አቅማቸውን በማጠናከር የህዝብ ጥያቄን በአግባቡ ለመመለስ ያስችላል'' ብለዋል።

ኢህአዴግ አደረጃጀቱና ተልዕኮውን አሳክቶ የጨረሰ ብቻ ሳይሆን ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይራመድ  በመሆኑ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ መለወጥ የህልውና ጉዳይ እንደሆነም ግንባሩ መግለጹ ይታወቃል።

ከቀናት በፊት የግንባሩ ሦስት ፓርቲዎች እና አምስት አጋር ድርጅቶች በይፋ ውህደት መፈጸማቸውን

  የስምንቱ ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርት በፊርማቸው አረጋግጠዋል።

ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት በማድረግ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ተመስርቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ /መድረክ/ የአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትመሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ107 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም