የኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋ የተሻለ እንደሚሆን ተገለጸ

64
ኢዜአ ህዳር 24/2012  በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሁኔታ  በተለያየ  ጎራየተሰለፉ ኃይሎች በአራት ጉዳዮች ላይ ተግባብተው የኢትዮጵያን መጻኢ ዕጣ ፈንታ ተንብየዋል። ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ጠንከር ያሉ ፈተናዎች ቢገጥሟትም መጻኢ ተስፋዋ የተሻለ መሆኑን የሚያመለክት የሊሆን ይችላል ምልከታ (ሴናሪዮ) ይፋ ሆኗል። በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ 50 ኢትዮጵያውያን ለስድስት ወራት ከተወያዩ በኋላ የአገሪቷን መጻኢ ዕድሎች የሚወስኑ ክስተቶችን ነው የገለጹት። ፕሮጀክቱን ‘በዴስቲኒ ኢትዮጵያ’ና ‘ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን’ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንዳስተባበሩትም ታውቋል። ‘በ 2032 የምንፈልጋት ኢትዮጵያ’ በተባለው በዚህ ክስተት ትንበያ ስብስብ ውስጥ ከተዋቂ ፖለቲከኞች እስከ ወጣት ምሁራን ድረስ ተሳትፎውበታል። የሴናሪዮ ቡድን አባላቱም ሲጀምሩ ለመግባባት እንደሚቸገሩ ገምተው እንደነበረና ከውይይቶች በኋላ ግን በተቃራኒው ተግባብተው መውጣታቸውን ተናግረዋል። በዚህም ከሃምሳዎቹ መካከል የ'ኦነግ' ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የ'አብን' ፕሬዚደንት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔና ሌሎች በተራራቀ የፖለቲካ አመለካከት ጽንፍ ላይ ከቆሙት ጋር ተሰባስበው ተግባብተው ወጥተዋል። በተሳታፊዎች ዘንድም የአቶ ዳውድ ኢብሳና የዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ተሳታፊ መሆንና ሁለቱ ግለሰቦች በሂደቱ ያሳለፉትን መመልከት ግርምትን ፈጥሮባቸዋል። ከነዚህ መካከል ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ''አቶ ዳውድ እና ዶክተር ደሳለኝ የቀልድ ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መመልከት ለኔ የልብ ወለድ ያህል ነው'' ይላል። ሌላዋ የቡድኑ አባል አርቲስት አስቴር በዳኔ በቡድን ቆይታዋ ''ሃሳብ እንጂ ሰው እንደማይራራቅ መረዳት ችያለው'' ብላለች። በዚሁ መሰረት ቡድኑ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ገምግሞ ወደ ፊት የሚያጋጥሙ እድሎችን በመዳሰስ የተሻለ ሁኔታ ይመጣ ዘንድ ምን መደረግ እንዳለበት የሚያመላክቱ አራት ምልከታዎችን(ሴናሪዮ) ይፋ አድርጓል። አንደኛው ሴናሪዮ በ’ሰባራ ወንበር’ የተመሰለ ሲሆን፤ ጠንካራ የሚመስል ግን የተልፈሰፈሰ አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ እንደምታልፍ አመላካች ነው ተብሏል። ሁለተኛው ደግሞ ‘አጼ በጉልበቱ’ የሚል ስያሜ የተሰጠውና "የማን አለብኝነትና የፈላጭ ቆራጭነት አገዛዝ እንደ አገር ሊገጥማት ይችላል" የሚል ግምት ተቀምጧል። ‘የፉክክር ቤት’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሴናሪዮ ደግሞ ክፍፍልና ክፍተቶች የበረቱበት፣ ኢኮኖሚው አድጎ ማህበራዊ ሁኔታው የተዳከመበት ኢትዮጵያ የተገመተችበት ነው። የመጨረሻው ሴናሪዮ ለየት ባለ መልኩ ‘ንጋት’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ኢትዮጵያ በመጪዎቹ 20 ዓመታት ቅራኔዎች በመግባባት የሚፈቱባት፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚገነባበት ትሆናለች የሚል ትንበያ ነው። ይህ የክስተት ትንበያው እውን ይሆን ዘንድም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለመታከት በአንድነት መስራት እንዳለበትም የሴናሪዮ ቡድን አባላት በአቋም መግለጫቸው አሳውቀዋል። አገሪቷ መንታ መንገድ ላይ መሆኗን ሁሉም ተረድቶ አዎንታዊው እጣ ፈንታ ይገጥማት ዘንድ ‘ንጋት” እውን እንዲሆን በጋራ መረባረብ ያስፈልጋልም ብለዋል። የፕሮጀክቱን ዓላማን በማስመልከት ማብራሪያ ያቀረቡት የፎረም ኦፍ ፌዴሬሽኑ አቶ ማዕረጉ ኃብተማሪያም ወሳኝ የተባሉ አካላትን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ችግሮችን በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚችሉ ማመላከት ነው ብለዋል። አቶ ማዕረጉ ፕሮጀክቱ ፅንፍ የወጡ የአገሪቷ የፖለቲካ አመለካከቶችን በማላዘብ ሰዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ልዩነታቸውን ጠብቀውና ተነጋግረው መግባባት እንደሚችሉ ያመላከተ እንደሆነም ነው የገለጹት። በተመሳሳይም የ'ዴስቲኒ ኢትዮጵያ' አስተባባሪው አቶ ንጉሱ አክሊሉም ሕዝቦቿ የሚፈልጓትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ጠንካራ ምክክር ተደርጓል ነው ያሉት። በዚህም የተለያዩ አስተሳሰቦች ተስተናግደውበት የቡድኑ አባላት የተግባቡበት የክስተት ትንበያው ይፋ መሆኑን አስታውቋል። እስካሁንም "ሳይቸግረን የተቸገርን፣ እያለን የሌለን የመሰለን ራሳችንን በሌላ ሰው ቦታ ማስቀመጥ ባለመቻላችን ነው'' ብለዋል ሚኒስትሯ። ፕሮጀክቱ ብዝሃነት በሰለጠነ መንገድ ከተስተናገደ ጸጋ እንጂ እርግማን አለመሆኑን በአግባቡ ለመረዳት የተቻለበት ነውም ብለዋል። በቀጣይም መንግስት አሁን የቀረቡትን ሃሳቦች በግብዓትነት የሚጠቀምና ለተግባራዊነቱ የሚተጋ መሆኑንም አረጋግጠዋል። መሰል ተሞክሮዎች ከዚህ በፊት በደቡብ አፍሪካም በሌሎች አገራትም የተሻለ ውጤት ማስገኘት ማስቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይም አራቱ ሴናሪዮዎች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ተመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም