በዋጋ መውደቅ ምክንያት ሰሊጥ ወደ ምርት ገበያ ድርጅት ማቅረብ አቋርጠናል - --ሰሊጥ አቅራቢ ነጋዴዎች

178
ኢዜአ ህዳር 24 / 2012 ዓ.ም በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን የሚገኙ ሰሊጥ አቅራቢ ነጋዴዎች በዋጋ መውደቅ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ያቀርቡት የነበረውን የሰሊጥ ምርት ማቋረጣቸውን ገለጸ። አቅራቢዎች እንዳሉት መንግስት ባስቀመጠው የመግዣ ዋጋ ተንተርሰው ለተከታታይ ወራት ከአምራቹ በመግዛት ለምርት ገበያ ድርጅቱ ቢያቅቡም ከፍተኛ ኪሰራ ስለደረሰባቸው ምርቱን ማቅረብ ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስረድተዋል። የሰሊጥ አቅራቢ አቶ በሪሁ ገብረ ስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ወራት ለምርት ገበያ ድርጅት  ባቀረቡት የሰሊጥ ምርት  80 ሺህ ብር ኪሳራ ደርሶባቸዋል፡፡ ባለፈው መስከረም ወር ለአንድ ኩንታል ሰሊጥ 4 ሺህ 400 ብር ገዝተው በምርት ገበያ ድርጅቱ መጋዝን ከ30 ቀን በላይ ለማቆየት ስለማይቻል ከአንድ ኩንታል ሶስት መቶ ብር በመክሰር እንደሸጡት ተናግረዋል። አቶ ልኡል ብርሃኔ  የተባሉ ሌላ አቅራቢ ደግሞ  ''እስካሁን በተስፋ እየከሰርንም ቢሆን ስናቀርብ ቆይተናል'' ብለዋል። አሁን ግን እዳ ያለበት አርሶ አደር ካልሆነ በቀር አምራቹም ለመሸጥ ፈቃደኛ ባለመሆኑ መደበኛ ስራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን አስረድተዋል። ''በተያዘው ህዳር ወር ብቻ ከ350 ኩንታል ሰሊጥ 105 ሺህ ብር ኪሳራ ደርሶብኛል'' ብለዋል። መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ተወካዮች በመምረጥ ወደ መቀሌና አዲስ አበባ መላካቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት የሁመራ የግብይት ማእከል መጋዝን አስተባባሪ አቶ ቢንያም ተክለ ብርሃን  ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ወደ ምርት ገበያ ማእከሉ እየቀረበ ያለው የሰሊጥ ምርት እየቀነሰ መሆኑን አምነዋል። ማዕእከሉ ባለፈው አመት ከሀምሌ እስከ ህዳር ወራት 245 ሺህ ኩንታል ወደ መጋዝን መግባቱን አስታውሰዋ በተያዘው አመት ተመሳሳይ ወቅት ግን 129 ሺህ ኩንታል ብቻ መረከባቸውን ገልጸዋል። ይህም ከ110 ሺህ ኩንታል በላይ ቅናሽ ማሳየቱን አስረድተዋል። ባለፈው አመት ህዳር ወር 189 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ወደ መጋዝን መግባቱን ያስታወሱት አስተባባሪው በተያዘው ህዳር ወር 54 ሺህ ኩንታል ብቻ ወደ መጋዘን መግባቱን ተናግረዋል። በኢፌድሪ ንግድ ሚኒስቴር የሰብል ምርቶች ግብይት ዳሬክተር አቶ  መስፍን  አበበ ቀደም ሲል ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ለኢዜአ በስልክ በሰጡት ምላሽ ሰሊጥ አቅራቢዎች በአለም አቀፍ ያለውን የሰሊጥ ገበያ በማገናዘብና ወደ ምርት ገበያ ድርጅቱ እንዲያቀርቡ መነገሩን ገልጸዋል፡፡ ይህን የተባለበት ዋና ምክንያት  ከዚህ  በፊት  በላኪዎች  የነበረ  ጤነኛ  ያልሆነ  የግብይት  ስርዓት  ህግና  ደንብ  ለመስያዝ ተብሎ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው አመት የነበረው የሰሊጥ ዋጋ በዓለም ከሚሸጥበት ዋጋ ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የሰሊጥ ዋጋ ከፍ ያለ እንደነበር ዳሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ግብይቱ ህግና ስርአት እንዲይዝ በመደረጉ ያለፈው አመት የነበረው የተጋነነ የሰሊጥ ዋጋ ለአሁኑ የሰሊጥ ዋጋ ተጽኖ ፈጥረዋል ብለዋል፡፡ ይህም ላኪዎች ሆን ብሎ በፈጠሩት የገበያ ሴራ በላኪነት ከተሰማሩበት ንግድ ስራ እንደከሰሩ ለማድረግ በተጋነነ ዋጋ በመግዛት ውጭ ገበያ ደግሞ በአነስተኛ ዋጋ በመሸጥ ችግር መፍጠራቸውን በወቅቱ ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ምእራባዊ ዞን በያዝነው የምርት ዘመን ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት መገኘቱን ኢዜአ መዘገቡን ይታወቃል። አሁን ያለው የሰሊጥ ዋጋ መውረድ ለሚቀጥለው የምርት ዘመን ከፍተኛ ተጽኖ ሊያሳድር እንደሚችል ከሁለት ሳምንት በፊት ኢዜአ መዘገቡን ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም