እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በ28ኛ እና 29ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሃግብሮች ላይ የቀን ለውጥ አድርጓል

68
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ28ኛ እና 29ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃግብሮች ላይ የቀን ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ ከዚህ በፊት ባወጣው መርሃግብር የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 18 እና 19 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲሁም የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳሉ ብሎ ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች የመርሃግብር ለውጥ ማድረግ በማስፈለጉ ምክንያት  የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2010 ዓ.ም የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚካሄዱ የሊግ ኮሚቴው አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከወልዲያ ከተማ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት፣ ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከፋሲል ከተማ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በክልል ከተሞች በአዳማ ስታዲየም ጅማ አባጅፋር ከደደቢት፣ በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከአዳማ ከተማ፣ በአርባምንጭ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ እንዲሁም በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከመቀሌ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በ29ኛው ሳምንት ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢት ከወልዲያ ከተማ ከቀኑ 9፡00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በክልል ከተሞች በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከመከላከያ፣ በመቀሌ ስታዲየም መቀሌ ከተማ ከኢትዮ-ኤሌትሪክ፣ በጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከአርባንጭ ከተማ፣ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ፣ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስና በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከጅማ አባጅፋር በተመሳሳይ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል። የሁለቱ ሳምንታት መርሃግብር ከመካሄዳቸው በፊት ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳሉ። በዚህም መሰረት በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ፣ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ይጫወታሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ደደቢት ከአርባምንጭ ከተማ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባ ጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 48 ነጥብ፣ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ መቀሌ ከተማ በ46 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ኢትዮ-ኤሌትሪክ፣ አርባምንጭ ከተማ እና መውረዱን ያረጋገጠው ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ናይጄሪያዊው የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ኦኮኪ አፎላቢ በ17 ግቦች እየመራ ሲሆን፣ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የኢትዮ- አሌትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም