ክፍለ ከተማውና ባለድርሻ አካላት ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፉን ለመደገፍ በሚያሰችል ሰነድ ላይ ተፈራረሙ

120
ህዳር 23/2012  የጉለሌ ክፍለ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ በሚያስችል ሰነድ ላይ በየደረጃው ከሚገኙ አካልት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ። የፊርማ ስነ-ስርዓቱ የተከናወነው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የክፍለ ከተማውና የወረዳዎች የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ  ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች በጋራ በመሆን ነው። ሰነዱ በዘርፉ የተሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ፤ ክትትልና ድጋፍ የማያደርጉ ባላድርሻ አካላትን ደግሞ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ነውም ተብሏል ። ከዚህ በፊት በዘርፉ የክትትልና ድጋፍ ስራዎቹ በአግባቡ ባለመሰራቱ 3ሺህ 648 የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ወደ ስራ ቢገቡም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት ግን 148 የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን  ከክፍለ ከተማው የተገኘው መረጃ አመላክቷል። በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ታደሰ ዘረፉ የሚፈለገውን ውጤት ያላመጣው በቂ የብድር አገልግሎት አለመኖርና አመች የሆነ የአሰራር ስርዓት ባለመዘርጋቱ እንደሆነ ተናግረዋል። የሚታየውን ችግር ለመፍታትም አሰራሮችን በመፈተሽና ማሻሻያ በማድረግ፤ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋትና የሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ የክትትልና ድጋፍ ስራ መስራት ሲችሉ ነው ብለዋል። የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍስሃ ክፍሌ በበኩላቸው የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል የሚሸፍን ስራ እንደሆነ ተናግረዋል። ዘርፉን የሚያንቀሳቅሱት ባለድርሻ አካላት ተገቢ የክትትልና ድጋፍ ባለማድረጋቸው፤ በስራው ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ሳይሰሩ በአቋራጭ ለመበልፀግ  ብለው በሚፈጥሩት ችግር የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አድርጎታል ብለዋል። ይህንን ችግር ለመፍታትም በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት የጋራ አሰራር ያስፈልጋል ተብሏል። በቀጣይም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን ችግሮች የመለየት ሰራ ከሰሩና ጠንካራ የሆነ ክትትልና ድጋፍ ስራ ከተሰራ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል። የጉለሌ ክፍለ ከተማ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም አባይነህ  በበኩላቸው ከዚህ በፊት ዘርፉን የሚያንቀሳቅሱ ባለድርሻ አካላትና  አሰፈፃሚዎች በጋራ የሚሰሩበት የድጋፍ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በቂ የሆነ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል። አሁን የተዘጋጀው ሰነድ የተሻለ ስራ የሚያሰራ መሆኑን በመግለፅ፤ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ በመጠቀም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የስምምነት ፊርማ ከተፈራረሙት የአራዳ ማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ ኮሌጅ ምክትል ዲን ኢንጅነር በቀለ ጎዳናው የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የትብብር ስራ የሚጠይቅና ብዙ ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢንጅነር በቀል አክለውም በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከተፈለገ  በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች   በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና መስጠት፤ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግና በትምህርት ላይ ላሉት ደግሞ ወቅቱ የሚጠየቀውን ትምህርት ማስተማር ሲቻል ነው ብለዋል። በገቡት ቃል መሰረትም ውጤታማ የሆነ ስራ  እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም