ከሁለት ሳምንት በላይ በመብራት መቋረጥ ምክንያት ለአላግባብ ወጪ መዳረጋቸውን የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አቀረቡ።

67
ህዳር 23/2012  ከሁለት ሳምንት በላይ በመብራት እጦት ምክንያት ለአላግባብ ወጪ መዳረጋቸውን ቅሬታቸውን ለኢዜአ ያቀረቡ በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ነዋሪዎች ተናገሩ። የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ችግሩ የተከሰተው አሮጌ መስመሮችን በአዳዲስ ለመተካት እየተሰራ በመሆኑ ነው ፤ ችግሩ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይፈታል ብሏል። ከሁለት ሳምንት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሾላ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የወረዳ 4 ነዋሪዎች ናቸው ቅሬታቸውን ያቀረቡት። ከነዋሪዎቹ  መካከል ወጣት እዮብ አየለ ነና ወይዘሮ አያልነሽ አበበ የመብራት ኃይል መቋረጡን ተከትሎ ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ በስልክና በአካል ጉዳዩን ቢያሳውቁም መፍትሔ እንዳልተሰጣቸውም ተናግረዋል። "ባለሙያዎች ችግሩን መጥተው አይተው እንሰራለን ካሉ በኋላም መፍትሔ ሊሰጡን አልቻሉም፤ ለእንግልትም እየዳረገን ነው" ብለዋል።የመብራት ዋጋ ክፍያን በወቅቱ በመክፈል ግዴታቸውን እየተወጡ ቢሆንም ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት በአግባቡ እያገኙ እንዳልሆነም ነው ኢዜአ ዋናው ግቢ ደረስ በአካል ቀርበው ቅሬታቸውን የተናገሩት። በተከታታይ ለ15 ቀናት ችግሩ እንዲፈታላቸው ባለሙያዎችንና የሚመለከታቸውን ሰዎች መጠየቃቸውን ገልጸውም፤ የሚሰጣቸውም ምላሽ ወጥና መፍትሔ አመላካች እንዳልሆነም ተናግረዋል። የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለሙያዎቹም "የመለዋወጫ መሳሪያ የለም"፣ "የሰው ኃይል እጥረት አለ" እና "በትዕግስት ጠብቁ" የሚሉ ምላሾችን እንደሚሰጡ ያስረዳሉ። በመብራት እጦት ምክንያትም በኢኮኖሚያቸው ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ችግር ውስጥ እንደገቡ ተናግረዋል። በመሆኑም ተጠቃሚው ህብረተሰብ ከምግብ ማብሰል ጀምሮ በመብራት የሚሰሩ የዕለት ከዕለት ስራዎችን ለማከናወን እንደተቸገሩና ለእለት ጉርስና ለኢኮኖሚ ድጎማ የሚውሉ ተግባራትን ማከናወን እንደ ቸገራቸው ተናግረዋል። በዚሁ ችግርም ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ነው የሚያብራሩት ነዋሪዎቹ። ስለሆነም ይህንን ችግር የሚመለከተው አካል ተገንዝቦ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። የኢዜአ ሪፖርተር የነዋሪዎቹን ቅሬታ ይዞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጠይቋል። የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪጅናል ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ በሰጡት ምላሽም የቀረበው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸው በአንድ ሳምንት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ችግሩ እንደሚፈታ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማሻሻል ፕሮጀክት ተቀርጾ ያረጁ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች በአዲስ እየተቀየሩ በመሆኑ ለጥንቃቄ ሲባል የኃይል ማቋረጥ እንደሚካሄድም ገልጸዋል። የፕሮጀክቶቹ ባለሙያዎች የማሻሻያ ሥራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅትም መብራት ከአምስት ሰዓት በላይ  እንዳያቋርጡና ስራቸውን ከጨረሱ በኋላ ኃይል በአግባቡ መልሰው እንዲለቁ ተነጋግረናል ብለዋል። በፕሮጀክት ሠራተኞችና በጥገና ባለሙያዎች መካከል ተናቦ መስራት ላይ ክፍተት እንዳለ ጠቁመው፤ ይህም እንዲታረም መደረጉንም ገልጸዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም