ኤች.አይ.ቪ ኤድስ እያስከተለ ያለውን አደጋ ለመግታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማሳደግ አንደሚገባ ተገለፀ

115
ህዳር 23/2012 ኤች.አይ.ቪ ኤድስ እያስከተለ ያለውን አደጋ ለመግታት ቫይረሱን በተመለከተ ያለውን መዘናጋት ማስቀረትና ሁሉን አቀፍ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተመከለተ ፡፡ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ “ ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የአለም ኤድስ ቀን አስመልክቶ በሀዋሳ ከተማ ከሚመለከታው አካላት ጋር የፓናል ውይይትና የተለያዩ መርሀ-ግብሮችን አካሂዷል ፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን በተመለከተ ሀገራዊና ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚያመላክቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ፡፡ የፓናል ውይይቱን የመሩት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ እንደገለፁት በክልሉ 70 ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች የቫይረሱን የስርጭት መጠን መቀነስ እንዲሁም የህክምና አገልግሎቶችንም በተገቢው መንገድ ማዳረስ መቻሉም ተናግረዋል ፡፡ በዚህም የበሽታውን የስርጭት መጠን በደቡብ ክልል ደረጃ  ወደ 0.4 በመቶ  መቀነስ ተችሎ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ባደረጉት ርብርብና በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አቅናው በአሁኑ ወቅት ግን የነዚህ አካላት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝና በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት የተገኘውን ውጤት ጥያቄ ውስጥ እየከተተው እንደሚገኝ አብራርተዋል፡ እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለፃ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ባለው መቀዛቀዝ የተነሳ የስርጭት መጠኑን ከተጠቀሰው አሃዝ ዝቅ ማድረግ ሳይቻል ቆይቷል ፡፡ እንደሀገር የተጋረጠውን አደጋ ለመግታት ደግሞ እየተስተዋለ ያለውን መዘናጋት ማስቀረት እንዲሁም ህበረተሰቡን በስፋት በማሳተፍ የተለየ የንቅናቄ ሥራ መሰራት እንዳለበት ገልፀዋል ፡፡ ለዚህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት ፡፡ ከጽሑፍ አቅራቢዎቹ መካከል ወይዘሮ ትዕግስት አሸናፊ በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት በተለይ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ፣ትምህርት ቤቶች ፣ የወጣት ማዕከላት ፣ ክበባት ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች ማህበራት እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ላይ የተሰሩ ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎች ቅድመ መከላከልና የአገልግሎት ተደራሽነት ከፍ እንዲል አስችለዋል ፡፡ ሚዲያዎችን በመጠቀም ይተላለፉ የነበሩ መልዕክቶችም ከፍተኛ ለውጥ አምጥተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ ተግባራዊ የሆነው የ“ ሜኒስትሪሚንግ ” ሥራም ሰራተኛው በተለይ የፖለቲካ አመራሩ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን አስመልክቶ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አድርጎት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በአሁን ወቅት ግን የእነዚህ ሥራዎች መዳከም በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እየተፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በተለይ በፖለቲካ አመራሩ ተግባራት መቀዛቀዝ ፣ የማህበረሰብ ውይይቶች መቋረጥና በህዝቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት ክፍተኛ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን ነው የተናገሩት ፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታትም በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያሻም ጠቁመዋል ፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ ተገኝተው የሕይወት ገጠመኞቻቸውን ካካፈሉ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውስጥ ከሚገኝ ወገኖች መካከል ወይዘሮ ዘነበች ቲሮሬ ከ19 ዓመታት በላይ ከቫይረሱ ጋር መኖራቸውን ተናግረዋል ፡፡ ላለፉት 19 ዓመታት ሌሎች ሰዎች ከሳቸው እንዲማሩና ራሳቸውን ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ እንዲጠብቁ ፣ ተመርምረው በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ መኖሩን ያወቁ ወገኖች ደግሞ በተገቢው መንገድ ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ሲያስተምሩ መቆየታቸውንም አስረድተዋል ፡፡ ለ20 ዓመታት ከቫይረሱ ጋር መቆቴ ሌሎች እንዲያዙ ምክንያት ሊሆን አይገባል ያሉት ወይዘሮ ዘነበች ኤች.አይ.ቪን ቀለል አድርጎ የማየትና የመዘናጋት ሁኔታዎች እየተስተዋሉ እንደሆነ ገልፀዋል ፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንተስኖት መልካ በበኩላቸው ኤች.አይ.ቪን በተመለከተ ከአራት ዓመታት በፊት በመጡ ለውጦች ተዘናግተን ቆይተናል ብለዋል ፡፡ በተያዘው ዓመት ከዚህ በፊት የነበሩ መቀዛቀዞችን ለማስቀረት ኃላፊነት ወስደን የንቅናቄ ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ የሚመለከታቸው የክልል ፣ የዞን እንዲሁም የልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም