ብልጽግና ፓርቲ ለአገራዊ አንድነትና ለሰላም መጠናከር ሚናው የጎላ ነው ---ደሴ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች

54
ህዳር 23 /2012 ዓ.ም ኢዜአ  የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የብልጽግና ፓርቲን እውን ለማድረግ መፈራረማቸው አገራዊ አንድነትንና ሰላምን ለማጠናከር ሚናዉ የጎላ ነው ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎችና የሐይማኖት አባቶች ገለጹ። የደሴ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ህሩያን ፍቀረኢየሱስ ተሰማ በሰጡት አስተያየት በውህደት የተመሰረተዉ ብልጽግና ፓርቲ በአገሪቱ እየታየ ያለውን ዉስብስብ ችግር ይቀርፈዋል የሚል እምነት እንዳሳደረባቸው ገልፀዋል ። የየድርጅቱ አመራሮች ትናንት በፊርማቸው የብልፅግና ፓርቲ እውን መሆን በፊርማቸው ማረጋገጣቸው ተስፋችን እንዲለመልም የሚያደርግ በመሆኑ  ከጎናቸው እንድንቆም አነሳስቶናል ብለዋል፡፡ ማንኛውም ሰው በአካባቢ ብቻ ከማሰብ ተላቅቆ አንድነትና ሰላምን እንዲሰብክ እምነታችን ያስተምራል ያሉት ስራ አስኪያጁ ለዚህ ደግሞ አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ አመቺ በመሆኑ ድጋፋችንን እንገልፃለን ሲሉ ተናግረዋል ። የደሴ ከተማ ጊዜያዊ መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሼህ እንድሪስ በሽር በበኩላቸው የብልጽግና ፓርቲን ለመመስረት የኢህአዴግ አባልና አጋር  ድርጅቶች ስምምነት መፈራረማቸው የውህደቱን ስሙርነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የፓርቲው ስምምነት መፈጸም በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰተውን የሰላም እጦት በማስቀረት የተረጋጋች ሀገር ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡ እምነታችን አንድነትን፤ ሰላምና መቻቻልን አብዝቶ ስለሚያስተምር በውህደቱ እውን መሆን ህብረተሰቡ በእጅጉ መደሰቱን ገልጸዋል፡፡ ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ይመር ሙሄ እንደገለጹት ውህደቱና ስምምነቱ አገራችን አሁን ወዳለችበት ችግር ከመግባቷ በፊት መፈፀም እንደነበረበት ተናግረዋል ። ምንም እንኳ ውህደቱ ቢዘገይም አሁንም ከገጠመን የመለያየትና የመሳሳብ  አባዜ በማላቀቅ የነበረውን የህዝቦች ትስስርና መፈቃቀር እሴት ለማጎልበት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል ። ውህደቱ ለኢትዮጵያ እድገትና ሰላም ሁሉም እኩል እንዲያስብ ከማድረጉም ባለፈ ስልጣን ተነፍገዉ የነበሩ ክልሎችን በማቀፉና በማሳተፉ የበላይና የበታች እንዳይኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡ ወጣት ኤርሚያስ ሰይፈ የተባለ የከተማው ነዋሪ በበኩሉ ውህደቱ በሁሉም ክልሎች እኩል የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል ብሏል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና የህግ የበላይነት እንደዲሰፍን በማድረግ በኩልም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ስለሚቀርፍ ከመንግስት ጎን እንድንቆም ያደርገናል የሚል አስተያየት ሰጥቷል ። ፓርቲው የአገር አንድነትን፣ የህዝቦቸ ትስስርንና መፈቃቀርን ለማስቀጠል በሚያደርገው ሁለንተናዊ ጥረት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም