የእስራኤሉ ጋሊሌ ዓለም አቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር ለመስራት ተስማሙ

53
ኢዜአ ህዳር 23/2012 የእስራኤሉ ጋሊሌ ዓለም አቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈጸሙ። በአዲስ አበባ በተካሄደው የመግባቢያ ፊርማ ስነ ስርዓት ላይ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደርና የሁለቱ ተቋማት ፕሬዝደንቶች ተገኝተዋል። የጋሊሌ ዓለም አቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ፕሬዝደንት ዶክተር ዮሴፍ ሼቭል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ "ኢንስቲትዩቱ በ 117 የዓለም ሀገራት ቅርንጫፎች ያሉት ትልቅ ተቋም ነው"። በዚህም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በግብርና በአስተዳደር ጥበብ ዘርፎች በርካታ ተማሪዎችን በማፍራት ውጤታማ ሆኗል ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የአጭርና ረጅም ጊዜ ስልጠና ከመስጠትም ባለፈ ከተለያዩ ተቋማት ጋርም በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያም ከሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር በአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ በትብብር ለመስራት ስምምነቱን መፈራረማቸውን ገልጸዋል። በተለያዩ የዓለም ሀገራት በርካታ የትብብር ስምምነቶች ቢፈረሙም አብዛኛዎቹ ተግባራዊ እየሆኑ አይደሉም ያሉት ፕሬዝደንቱ፤ "የተስማማንባቸውን ጉዳዮች እንዴት እንተግብረው?" የሚለው ዋናው ትኩረት መሆኑንም ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላቸውም ገልጸው፤ በቀጣይም በትምህርትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። የሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝደንት ዶክተር ተረፈ ፈይራ በበኩላቸው የሁለቱ ተቋማት ትብብር "ከአጫጭር ሰልጠናዎች እስከ የጋራ ተቋም ግንባታ የሚዘልቅ ነው" ብለዋል። በአጭር ጊዜ እቅድ የጋሊሌ ዓለም አቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ፕሮፌሰሮች መጥተው እንዲያስተምሩና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እናደርጋለንም ብለዋል። ከኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ጋር በማይጋጭ መልኩ የጋራ የሆነ ስርዓተ ትምህርት ለመቅረጽም እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማሳደግ በኢትዮጵያ ግዙፍ የኢትዮ-እስራኤል የትምህርት ተቋም የመገንባት ራዕይም ሰንቀናል ብለዋል። በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭም "የሁለቱ ሀገራት ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል። በጋሊሌ ዓለም አቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትና በኢትዮጵያ ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መካከል የተፈረመው ስምምነትም ለሌሎች ዘርፎች በር ይከፍታል ብለዋል አምባሳደሩ። ሁለቱ አገራት በተለይም ግብርናን ከሚያዘምኑ ልዩልዩ ድጋፎች በተጨማሪ በሌሎችም ዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች አሏቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም